የድሬደዋ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

0
91
የኖብል ኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም ከፍተኛ አደጋ በደቀነበትና ስጋት በፈጠረበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። የቫይረሱ መተላለፊያ መንገድ ከመቀራረብና ከንክኪ ጋር የተገናኘ መሆኑ የእለት ተለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተለመደው መንገድ እንዳይከናወን ተፅእኖ እያሳደረም ይገኛል።
ቫይረሱ እያስከተለ ካለው የሞት አደጋ ባሻገር በአለምአቀፍ ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲገታ ያደረገ ሲሆን ቀላል የማይባል ስነልቦናዊ ጫናም እየፈጠረ ይገኛል ።
የኮረና ቫይረስ ወደአገራችን መግባቱ በይፋ ከተገለፀበት ጊዜ ጀምሮ ቫይረሱ ወደ አስተዳደራችን እንዳይገባ ለመከላከልና ከገባም በህዝባችን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር እንዲቻል የተለያየ የቅድመ መከላከል ዝግጅት ሲከናወን ቆይቷል።
የቅድመ መከላከል ስራውን በተቀናጀ ሁኔታ ለማከናወን እንዲቻልም የሚመለከታቸው የአስተዳደሩና የፌደራል የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት
በአስተዳደሩ ከንቲባ የሚመራ ግብረሀይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።
በአስተዳደር ደረጃ እየተሰራ ያለውን የቅድመ መከላከል ስራ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል የአገር አቀፉን የመንግስት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ የሚከተሉት የጥንቃቄ እርምጃዎችና ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ በግብረ ሀይሉ ተወስኗል ።
በመሆኑም ማንኛውም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እነዚህን የጥንቃቄ እርምጃዎችና ማሳሰቢያዎችን በመፈጸም ሰብዓዊና አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ግዴታ የተጣለበት መሆኑን እናሳውቃለን ።
1ኛ) በአስተዳደሩ በአጠቃላይ በተለይም በከተማ ያለውን ሰፊ የሰዎች እንቅስቃሴ በመቀነስ የቅድመ መከላከል ስራውን ለማጠናከር ሲባል የህመም ችግር ያለባቸው ፣ እድሜያቸው የገፋ ፣ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ ሴት የመንግሥት ሰራተኞች በቀጥታ በቤታቸው እንዲቆዩ ተወስኗል ። በተጨማሪም ሌሎች በቤታቸው መቆየት ያለባቸውንና በቤታቸው ሆነው ስራቸውን መስራት የሚችሉ ሰራተኞችን በተመለከተ በየተቋማቱ የማኔጅመንት ኮሚቴ ውሳኔ እንዲሰጥ ተወስኗል ።
2ኛ) ትራንስፖርት ፦
የድሬዳዋ ከተማ አውቶቡስ ፦ በወንበር ከመጫን አቅሙ በግማሽ ቀንሶ እንዲጭንና የንፅህና መጠበቂያ ግብአቶችን አሟልቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ተወስኗል ።
የመንግስት መስሪያ ቤት ሰርቪሶች፦
በወንበር ከሚጭኑት መጠን በግማሽ ቀንሰው በምልልስ ሰርቪስ እንዲሰጡ ተወስኗል ። በተጨማሪም ከስራ መውጫና መግቢያ ሰአት ውጪ ባለው ጊዜ በሚመደብላቸው ቦታ ተገቢውን የጥንቃቄ ግብአቶች አሟልተው በነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ተወስኗል ።
በግል በህዝብ ትራንሰፖርት ስራ ላይ የተሰማራችሁ ወገኖች
የተሳፋሪውን ቁጥር ከተፈቀደው የመጫን መጠን በመቀነስ መተፋፈግ እንዳይፈጠርና
በተሳፋሪዎች መካከል በቂ ርቀት እንዲኖር በማድረግ ተገቢውን አገልግሎት እንድትሰጡ እያሳሰብን ይሄን በማይፈፅሙ አካላት ላይ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን እንገልፃለን።
3ኛ) ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም አይነት ስብሰባ ፣ ሰርግ ፣ ተስካር የመሰሉ ሁነቶችን ማካሄድ በጥብቅ የተከለከለ ነው። ሆኖም አስቸኳይና የግድ መሰብሰብን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በአስተዳደሩ ጤና ቢሮ በሚሰጥ እውቅናና ፍቃድ ከ20 የማይበልጡ ተሳታፊዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማሟላትና ተገቢውን ርቀት ጠብቀው እንዲቀመጡ በማድረግ ሊከናወን ይችላል።
4ኛ) በሁሉም የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ፣ ጤና ጣባያዎችና ክሊኒኮች ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን ከአንድ በላይ አስታማሚ ማስገባት የተከለከለ ነው፡፡
5ኛ) የስፖርት ውድድሮች፣ የአካል ብቃት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ መዋኛ ቦታዎች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የመዝናኛ እና የመጫወቻ ስፍራዎች ላልተወሰነ ጊዜ
አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ ተወስኗል ።
6ኛ) ትምህርት ቤቶች የተዘጉት ተማሪዎችና መምህራን በቤታቸው እንዲቀመጡና ለበሽታ እንዳይጋለጡ በመሆኑ ማንኛውም ተማሪና መምህር በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከቤት ባለመውጣት እየተደረገ ላለው የቅድመ መከላከል ጥረት አጋዥ እንድትሆኑ እናሳስባለን ።
የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ በይፋ እስካልተፈቀደ ድረስ በአስተዳደሩ የሚገኝ ማንኛውም የትምህርት ተቋም ተዘግቶ እንዲቆይም ተወስኗል።
7ኛ) ማረሚያ ቤት፣ የህፃናት ማሳደጊያ ፣ የአረጋውያን መጦሪያና መሰል ድርጅቶች ውስጥ ቫይረሱ ከገባ የከፋ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ በተለየ ሁኔታ ፍፁም የሆነ የቅድመ መከላከል ጥንቃቄ እንዲደረግ በጥብቅ እናሳስባለን።
8ኛ) የመሳሳምና የትከሻ ሰላምታን ጨምሮ እጅ መሳምና መጨባበጥን
የመሰሉ አካላዊ ንክኪ ያላቸው የሰላምታ አይነቶችን በመተው ፣ ከአንገት በላይ የሚገኝ የአካል ክፍልን ከመንካት በመቆጠብና
ቶሎ ቶሎ እጅን መታጠብን የመሰሉ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ኮሮናን ለመከላከል ወሳኝ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ራሳችንን ፣ ቤተሰባችንንና ማህበረሰባችንን ለሞት ከሚዳርግ በሽታ የመጠበቅ ሃላፊነታችንን በቅን ልቦና ልንወጣ ይገባል ።
9ኛ) በጣም አስፈላጊና የግድ ካልሆነ በስተቀር ወደ ገበያና ሰው የሚበዛባቸው ቦታዎች አዘውትሮ አለመሄድ ይገባል ። ከተሄደም ማህበራዊ ርቀትን በመጠበቅና መቀራረብን በመቀነስ ጉዳይን መፈፀም ይገባል ።
ወደ ቤት ሲመለሱም እቤት ከመግባት ልጆችን ከማቀፍና ሌሎች እቃዎችን ከመንካት በፊት እጅን በደንብ መታጠብ፤ እንዲሁም የተገዙ ቁሳቁሶችን ከመጠቀም በፊት በአግባቡ በማጠብ ለቫይረሱ የመጋለጥ አጋጣሚዎችን ለማስወገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ።
10ኛ) የእምነት ተቋማት ፦
ከዚህ በፊት ከየእምነት ተቋማቱ አባቶች ጋር በተደረገው ውይይት በተደረሰው መግባባት መሠረት የእምነት ስርአቶች ከተገቢው ጥንቃቄ ጋር እንዲፈፀሙ ጥሪ እናቀርባለን ።
በተጨማሪም ኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሰው ዘር ላይ የደቀነውን አስከፊ አደጋ በውል በማጤን የሁሉም እምነት ተቋማት አባቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረግ ያስቀመጡትን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የቅድመ መከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን እንዲደረግ አደራ እንላለን ።
11ኛ) በአገር ላይ የመጣውን መጥፎ አጋጣሚ ከሀይማኖትና ከህግ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በተለያዩ እቃዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በሀይማኖት ሀጢያት በህግም ወንጀል ነው። የዚህ አይነት ህገወጥ ተግባር የሚፈፅም ማንኛውም አካል
ከዚህ አፀያፊ ተግባር እንዲርቅ እያስጠነቀቅን ይህን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ እናስታውቃለን ።
12ኛ) በከተማም ሆነ በገጠር የምትኖሩ የአስተዳደራችን ነዋሪዎች
አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ከከተማ ወደ ገጠር ፤ ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከክልል ወደ ክልል፣ ከሀገር ወደ ሀገር ጉዞ ከማድረግ እንድትቆጠቡ እናሳስባለን።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከየትኛውም አካባቢ በተለይም የቫይረሱ ምልክት ከታየባቸው አካባቢዎች
ወደ ድሬዳዋ የመጣችሁና ወደፊትም የምትመጡ ሁሉ በተቻለ አቅም ለ14 ቀናት ያህል እንቅስቃሴያችሁን ቁጥብ በማድረግና ሕዝብ በሚበዛበት ቦታ ባለመገኘት ሕዝባችሁን ከአደጋ የመጠበቅ አገራዊ ሀላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ።
ይሔ ከሆነ ለቫይረሱ የመጋለጥ አጋጣሚ ቢኖር እንኳን እንቅስቃሴያችሁ ውስን ከሆነ ከናንተ የተገናኙ ሰዎችን በቀላሉ መለየት ስለሚቻል የበሽታውን የመስፋፋት ፍጥነት በቶሎ ለመግታት የሚያስችል ስለሚሆን ለመከላከል ስራው ተባባሪ እንድትሆኑ በጎ ፈቃዳችሁን እንጠይቃለን ።
13ኛ) በመጠጥ ቤቶች፣ በምሸት ጭፈራ ቤቶች ፣ በሺሻ ቤቶችና በሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲቆም ተወስኗል ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከጅቡቲ ተመልሰው በደወሌ የነበሩ 814 ዜጎች ከድሬዳዋ 5 km ርቀት ላይ በለይቶ ማቆያ ቦታ እንዲቆዩ መደረጉ በመግለጫው ላይ ተገልጿል። የቆይታ ጊዜያቸውን ሲጨርሱም ትራንስፖርት ተዘጋጅቶ ወደየአካባቢያቸው ይመለሳሉ ተብሏል።
በመጨረሻም የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ላይ የደቀነውን ከባድ አደጋ መቋቋም የምንችለው ከተከሰተ በኋላ ሳይሆን ከመከሰቱ በፊት ባለው የቅድመ መከላከል ተግባር በመሆኑ ሁሉም ሕዝባችን ሳይረበሽ ከትክክለኛ የመረጃ ምንጮች የሚሰጡትን የጥንቃቄ እርምጃዎች አድርጉ የተባለውን ሙሉ በሙሉ በማድረግና አታድርጉ የተባለውን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ባለመድረግ ታላቅ አገራዊና ወገናዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን ።