“ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም የህዝብን ጥቅምና ፍላጎትን ያገናዘበ ነው” የድሬዳዋ እና የሀረሪ ክልል አመራሮች

0
57
በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ፍላጎትና ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ካለማንም ጣልቃ ገብነት በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተሳትፏችንን እናጎለብታለን ያሉት በሀረር ከተማ ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የድሬዳዋ እና የሀረሪ ክልል የብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ናቸው::
ከአመራሮቹ መካከል ወ/ሪት አሊያ ሁሴን እንደተናገረችው “በተለይም አሜሪካ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የማስማማት ሚና መወጣት የነበረባት ቢሆንም ለሌሎች የወገነና በኢትዮጵያ ጥቅምና መብት ላይ ተፅእኖ የሚያሳድር አቋም መያዟ ተገቢ አይደለም፡፡” ብላለች
እንደ ወይዘሮ አሊያ ገለፃ በአባይ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከተሳትፎ እስከ መስዋዕትነት የሚደርስ ቆራጥነነት ነው ያለው በመሆኑ በቀጣይ ህዝቡን በማነቃነቅ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት ማድረግ ይገባዋል ብላለች፡፡
አቶ አብዱረዛቅ አህመድ በበኩሉ “የተፈጥሮ ሃብታችንን የማበልፀግና የመጠቀም ሙሉ መብት አለን” ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም ተገቢና የሚደነቅ ነው፡፡ ከጅምሩ ጀምሮ በግድቡ ላይ ሁሉም የራሱን አሻራ ያሳርፏል አሁንም ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ሲል አስተያየት ሰጥቷል::
አመራሮቹ በአስተያየታቸው የተቀዛቀዘ የሚመስለው የህዝብ ተሳትፎ እንዲጎለብት ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ ህዝቡም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ድጋፉን በአባይ ግድብ ላይ አሻራውን እንዳኖረ ሁሉ አሁንም አጠናክሮ በመቀጠል ከመንግስት ጎን መቆም ይገባል ብለዋል፡፡
ከአመራሮቹ መካከል አቶ አብዲ ኢብራሂም እንዳሉት አሜሪካ ከግድቡ ውሃ አሞላል ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊና አግባብ ያልሆነ ተፅእኖ እያደረገች ቢሆንም መንግስት የያዘው አቋም የህዝብን ጥቅምና ፍላጎትን ያገናዘበ ነው ብለዋል፡፡
አባቶቻችን አድዋ ላይ ገድል እንደሰሩ ሁሉ አሁን ያለው ትውልድም አንድ ሆኖ በግድቡ ላይ በመረባረብ ዳግም ታሪክ መስራት ይገባዋል ብለዋል፡፡
አባይ ግድብ ግንባታ እዚህ እንዲደርስ እናቶ ቅጠል ሽጠው ፅዳት ሰርተው አሻራቸውን አኖረውበታል፤ እንዲሁም ተማሪ ህፃናት ሳይቀሩ ተሳትፈውበታል ያሉት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትግስት ሙሉጌታ ናቸው፡፡
በመሆኑም ግድቡን እንደጀመርነው ሁሉ እንጨርሰዋለን፤ ለዚህም በግሌ ተሳትፎዬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብለዋል፡፡ አያይዘውም ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር የንቅናቄ ስራ መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሃብታችንን ለመጠቀም የማንንም ፍቃድ ማግኘት አይጠበቅብንም ያሉት ደግሞ አቶ ሀሰን ኢብራሂም ናቸው፡፡ ግድቡ በራሳችን አቅምና በህዝባችን የነቃ ተሳትፎ የጀመርነው ፕሮጀክት ነውም ነው ያሉት::
እያንዳንዷ ድሃ እናቶች ተሳትፎ ባደረጉበት የአባይ ግድብ ግንባታ በምንም መልኩ እንደማይስተጓጎል ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡ “ግድቡ የኔ ነው፤ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ፕሮጀክት ነው፤ በመሆኑም በማንም ተፅዕኖ የግድቡ ስራ አይቆምም” ሲል ተናግሯል፡፡
መንግስትም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዘው አቋም የህዝብን ጥቅምና ፍላጎትን ያገናዘበ በመሆኑ ግድቡ ካለምንም ችግር በታቀደው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንጥላለን ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡