ህዝበ ክርስትያኑና ህዝበ ሙስሊሙ የመከባበርና የመፈቃቀር ባህላቸውን በድምቀት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ማሳየት እንዳለባቸው ተገለፀ ፡፡

0
56

የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ ጣሀ እንደገለፁት የጥምቀት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ከመሆኑም ባሻገር በዩኔስኮ በአለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ይህ ደማቅ በዓል በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር ከሐይማኖት አባቶች፣ ከመንግስት ባለስልጣናትና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይት መደረጉንም ገልፀዋል፡፡

 

ድሬዳዋ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተከባብረውና ተፈቃቅረው የሚኖሩባት እንደመሆኗ መጠን የክርስትናም የእስልምናም እምነት ተከታዮች በጥምቀት በዓልም ይህን አኩሪ ባህል እንዲያስጠብቁ አቶ ሙሳ ጠይቀዋል፡፡

 ህብረሰተቡም በበዓሉ አከባበር ላይ ችግር የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ካየ ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቶ ሙሳ አሳስበዋል፡፡

 የድሬዳዋ የሐይማኖት ተቋማት ሰብሳቢ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው በበኩላቸው የጥምቀት በዓል የደስታና የፍቅር መንፈሳዊ በዓል መሆኑን ጠቅሰው እንደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዓሉ በክርስቲያኖች ዘንድ ለብዙ ሺ ዓመታት በሰላም እንደተከበረና ይህ በዓል የእምነት በዓል ስለሆነ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባህር ገብቶ ሲጠመቅ የሰው ልጆችን ሐጥያት በጥምቀት ይቅር ያለበት በመሆኑ ክርስቲያኖች በዓሉን በደስታ፣ በፍቅር በመቻቻል ማክበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

 የድሬዳዋ እስልምና ምክር ቤት ፀሃፊ ሼክ ኢብራሂም እንደ እስልምና እምነት ጉዳዮች በኃይማኖት ተቋማት አማካኝነት ሙስሊሙም ክርስቲያኑም አብሮ በመስራት አመታዊ በዓሉን አብሮ በማክበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡

በትግስት ቶሎሳ