ብስክሌትን የትራንስፖርት አማራጭ የማድረግ ባህል እንዲዳብር ጥሪ ቀረበ ከ55 ዓመታት በላይ የክስ ሪከርድ የሌለባቸው አሽከርካሪዎች ተሸልመዋል፡፡

0
54

ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 22/2012 መንገድ ላይ የሚደርስ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ታስቦ ሲካሄድ የቆየው የንቅናቄ ፕሮግራም ማሣረጊያውን የከተማዋን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ብስክሌት በመሸለምና ለበርካታ አመታት ምንም አደጋ ሳያደርሱ ህግን ባለመተላለፍ ላሽከረከሩ ሹፌሮች የሜዳሊያና የእውቅና ሰርተፍኬት በመስጠት ማሣረጊያውን አድርጓል፡፡ ህብረተሰቡም ብስክሌትን እንደ አማራጭ ትራንስፖርት በመጠቀም የትራፊክ መጨናነቅን እንዲቀንስ ጥሪ ቀርቧል፡፡ የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በጋራ ባዘጋጁት በዚሁ ፕሮግራም 20 የሚሆኑ ብስክሌቶች በ2 ማህበራት ለተደራጁ 20 ወጣቶች በስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፤ የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እንደተናገሩት እነዚህ ብስክሌቶች የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ፣ የአየር ብክለትን በማስቀረትና ጤናማ ህብረተሰብን በማፍራት የሚኖራቸው ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ ለወጣቶችም የሥራ እድልን በመፍጠር የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ አህመድም የድሬዳዋ ከተማና ብስክሌት የነበራቸውን ታሪካዊ ቁርኝት አውስተው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከከተማዋ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪን እንደ አማራጭ እየተጠቀመ ያለበትን ሁኔታ ገልፀዋል፡፡

መንግስት በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች መካከል በ5ቱ ጭስ አልባ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮችን ለመተግበር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ከንቲባው ከነዚህ ከተሞች መካከልም ድሬዳዋ አንዷ መሆኗን ገልፀዋል፡፡ የብስክሌት አገልግሎት ሙከራ ትግበራው ላይ ከፌደራል የመጡ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ከንቲባው፣ የፖሊስ ኮሚሽነሩ እንዲሁም ሚኒስቴር ዴኤታዋ በጎዳና ላይ ብስክሌቶቹን በመንዳት ለህብረተሰቡ አሣይተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የመንገድ ላይ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እንዲቻል ወሩን ሙሉ ሲካሄድ የነበረው ንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ ላይ በአቶ ኤፍሬም ገቢሳ፤ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የመንገድ ትራፊክ አደጋ ትናንት ዛሬና ነገ የሚገልፁና ለታዳሚ እንግዶች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም እንግዶችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም ለበርካታ አመታት በግልም ሆነ በሹፌርና ስራ ተሰማርተው ህግን በማክበርና በጥንቃቄ በማሽከርከር ምንም አይነት ሪከርድ የሌለባቸው ተብለው የተመረጡ ግለሰቦችን እውቅና ሠርተፊኬት በሜዳሊያ ሽልማት በማበርከት መርሀ ግብሩ ተጠናቅቋል፡፡