ባለፉት 3 ወራት የ14 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ ጠፍቷል ባሳለፍነው አመት በመንገድ ላይ በሚፈፀም የትራፊክ አደጋ7 መቶ 44 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል 31 ዜጎች ህይወታቸው አለፋል ይህ አደጋ እያስከተለ ያለው ጉዳት እያሻቀበ መሆኑን ማሳያው ደግሞ አሁንም በአስተዳደሩ ባለፉት 3 ወራት ብቻ የ14 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ ማለፉ ነው፡፡

0
45

በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋ የንቅናቄ ስራዎች እየተሰራ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በድሬዳዋ አስተዳደር የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤትም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚረዱ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ከታህሳስ 07 እስከ 22/2012 ዓ.ም የሚቆይ የንቅናቄ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስሜነህ ለማ የትራፊክ አደጋን አስመልክቶ በተናገሩት ንግግር በአለማችን ካሉት መኪኖች 100% በአህጉራችን የሚገኘው 1 % ሲሆን 98 % አደጋ የሚደርሰው ግን በኛ አህጉር ነው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በፍጥነት ማሽከርከር ሲሆን በ2011 ዓ.ም በሀገራችን ኢትዮጲያ 4597 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህም ጋር በማያያዝ የአደጋውን አስከፊነት በመገንዘብ በምስራቅ ሀረርጌ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ባለበት ለመግታት ህግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ እርምጃ መውሰድ ለነገ የምንለው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ገቢሳ በመንገድ ላይ ትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለው ጉዳት ዋና መንስኤ ፍጥነት በመሆኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 14 ሰዎች የአደጋ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ካሳለፍነው አመት ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ መጨመሩን ያሳያል ፡፡ የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በይመለከተኛል ስሜት የመንገድ ስርዓቶችን አክብሮ ሊንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም አክለውም የትራፊክ አደጋ ቀጥተኛ የሆኑ ባለድርሻ አካላቶችን ብቻ በሚሰሩት ስራ ለውጥ የሚመጣ ባለመሆኑ ከሌሎች ክልሎች ባገኘነው ልምድ በመነሳት የፖለቲካ አመራሮች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት እንቅስቃሴ በአስተዳደሩ እንዲኖር መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በሹፍርና ስራ ይተዳደሩ የነበሩት አቶ አጫዋች ኤርቦሎ በትራፊክ አደጋ ሁለት እግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በስራቸው የሚያስተዳድሩትን ቤተሰብ ለ8 አመታት ማስተዳደር ባለመቻላቸው በሰዎች እርዳታ አየኖሩ መሆኑን በመግለፅ በሳቸው ላይ ጉዳት ያደረሰ አሽከርካሪ ከመጠን በላይ በሆነ ፍጥነት በማሽከርከር በመሆኑ አሽከርካሪዎች ትራፊክ ፖሊስን በመፍራት ሳይሆን ህግን በማክበር የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ዋጋ ሊሰጡት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በድል ጮራ ሆስፒታል የኦርቶ መቲክ ክፍል አስተባባሪ ሲስተር ዮዲት ካሣ የትራፊክ አደጋ በሚያደርሰው ጉዳት በሆስፒታሉ ያሉ የአጥንት ክፍል አልጋዎች በብዛት እንደሚያዙ ገልፀው፤ ይህ ደግሞ አደጋው ምን ያክል ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ አብዛኛው የአደጋ ተጎጂዎች የአካል መጉደልና የአልጋ ቁራኛ እንዲሁም ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የተናገረችው ሲስተር ዮዲት አሽከርካሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ ይህን አስከፊ ጉዳት በማሰብ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ “እንደርሳለን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ የንቅናቄ ዝግጅት በከተማዋ በማርሽ ባንድ በመታገዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ፣ የሳይክል ውድድርና የደም ልገሳ እንዲሁም በድል ጮራ ሆስፒታል የአደጋ ተጎጂዎችን ቀን ማክበርና ተጎጂዎችን የመጎብኘት መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም በአራት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የትራፊክ አደጋን አስመልክቶ የጥያቄና መልስ ውድድርና በከተማዋ በ4 በተመረጡ ቦታዎች በስክሪን የአደጋውን አስከፊነት የሚገልፁ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ለነዋሪው ለማሳየት መታቀዱ ተገልጿል፡፡