በአስተዳደሩ ውስጥ ለሚገኙ 82 የኃይማኖት ተቋማት ለሚያስተዳድሯቸው የቤተ-እምነት ስፍራዎች ህጋዊ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ

0
61

በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ 9 የኦርቶዶክስ አቢያተክርስቲያናት፣ 66 የሚስሊም መስጊዶች እና 7 የፕሮቴስታንት አቢያተክርስቲያናት በአጠቃላይ 82 የሀይማኖት ተቋማት የመሬት ይዞት ማረጋገጫ ካርታ ከአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ተረክበዋል፡፡ በካርታ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋን ጨምሮ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ደራራ ሁቃ እንዲሁም ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ የድርጅትና የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የሁሉም የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮችም በስፍራው በመገኘት የይዞት ማረጋገጫ ካርታውን ተረክበዋል፡፡ በእለቱ ንግግር ያረጉት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እንደገለፁት አስተዳደሩ በዚህ መልኩ ለሁሉም የሀይማኖት ተቋማት በአንድ ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠት ያስፈለገው ተቋማቱ ከ70 አመታት በላይ ሲጠይቁ ለነበረው ትክከለኛ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው አክለውም በተለይም በሀገራችን የለውጥ ጉዞ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት ሂደቱና ለማደናቀፍ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ህዝቡን ለማጋጨት እየሰሩ የቆዩ መሆናቸውንና አሁን ደግሞ በተለየ መልኩ የሀይማኖት ግጭትን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ በአስተዳደራችን የሚገኙ የእምነት ተቋማት ለዚህ ችግር በር የሚከፍቱ ጉዳዮችን ቀድሞ ለመዝጋትም ያለመ ተግባር መሆኑንን ገልፀው በቀጣይም ቤት ተከራይተው ሀይማኖታዊ ክዋኔዎችን ለሚፈፅሙ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም መሬት እንዲያገኙ ይሰራልም ብለዋል፡፡ የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ደራራ ሁቃ በኩላቸው የአስተዳደሩ ካቢኔ ለሀይማኖት ተቋማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ተቋማቱ በያዙት የመሬት ስፋት ልክ ምንም ሳይቀነስባቸው ህጋዊ ማረጋገጫ እንዲሰታቸው በወሰነው መሰረት ለማምለኪያና ለመቃብር ስፍራዎቻቸው ካርታው እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች ሰሞኑን በአማራ ክልል ሞጣ ወረዳ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት የክርስቲያንንም ሆነ የእስልምና እምነት ተታዮችን እንደማይወክል እና በጥፋት ሀይሎች የተፈፀመ መሆኑን ገልፀው ድርጊቱን አጥብቀን እናወግዛለንም ብለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች በከተማችን እንዳይከሰቱ የሀይማኖት ተቋማት ህዝቡን የማስተማር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በዚሁ አግባብ ጠንክረው እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው ለቤተእምነቶቻቸው የይዞታ ማረጋገቻ ካርታ በማግኘታቸው እንደተደሰቱና በተለይም ለሁሉም የሀይማኖት ተቋማት አንድ ላይ መሰጠቱ ደስታቸውን ድርብ እንደሚያደርገው ሲሆን የኢፌዴሪ ጠ/ሚንስተር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዲ/ን ዳንኤል ክብረትም በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ተግባሩም ድሬዳዋ የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት መሆኗን ያረጋገጠ ነው ሲሉም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡