“በህብር ወደ ብልፅግና” የምሁራን የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

0
153

በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምሁራን ቀደም ሲል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎና በመንግስትም የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚደረገው ጥረት አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ይሁንና ይህን ሰፊ ክፍተት የተረዳው መንግስት ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮም ይህን አገራዊ ክፍተት በመረዳትና የምሁራንን አይነተኛ ሚና በመገንዘብ ምሁራንን ያሳተፈ “በህብር ወደ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ከምሁራን ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከንቲባው አማካሪ የሆኑት አቶ ብሩክ ግዛው የኢህአዲግ ውህደት አግላይ የነበረውና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን በፖለቲካ ውስጥ አነስተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርግ የነበረውን ስርዓት አስቀርቶ ንቁ ተሳታፊና በውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ሚናቸውን የሚያጎላ ነው ብለዋል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ትክክለኛ የሆነ የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዲኖር የሚታገል እንደሆነ የገለፁት አቶ ብሩክ ይህን የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለማስፈን እየሰራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት በማረጋገጥና ብዝሃነትን በመጠበቅ የፌዴራል ሥርዓቱን ማጠናከር ይቻላል ያሉት አቶ ብሩክ የጋራ የሆኑ ብዙ ጉዳዮች አሉንና የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ አጠንክረን በመስራት ለፌዴራል ሥርዓቱ መጠንከር አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡ የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ብልፅግና ፓርቲ ያነገበው ዓላማ መሆኑን በመግለፅ የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከታከለበት ይህን ዓላማ ለማሳካት እንደሚቻል በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በውይይት መድረኩ ላይ ሀሳባቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ተሳታፊዎቹ ቀደም ሲል የምሁራን በአገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ውስንነት እንደነበረው በመግለፅ አሁን ይህ የውይይት መድረክ ምሁራንን አሳታፊ መሆኑን አድንቀዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ቀጣይነት እንዲኖረው በመጠቆም፡፡