“በህብር ወደ ብልፅግና” የምሁራን የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

0
45

ምሁራን ቀደም ሲል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎና በመንግስትም የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚደረገው ጥረት አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ይሁንና ይህን ሰፊ ክፍተት የተረዳው መንግስት ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮም ይህን አገራዊ ክፍተት በመረዳትና የምሁራንን አይነተኛ ሚና በመገንዘብ ምሁራንን ያሳተፈ “በህብር ወደ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ከምሁራን ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምሁራንን ያማከለና ለምሁራን ክፍት ካለመሆኑ የተነሳ በአገራችን ምሁር መር ፖለቲካ ነበረን ማለት አይቻልም ያሉ ሲሆን ያለ ምሁራን እውነተኛና ቀጥተኛ ተሳትፎ ደግሞ ከግጭት የራቀና በልማትና ዲሞክራሲ ላይ የሚያተኩር የተረጋጋ ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም ብለዋል፡፡ አሁን በአገራችን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ምሁራን በጥናትና በምርምር ላይ የተመሰረተ የሀሳብ ልዕልና እንዲጎለብት፣ የህዝብ ኑሮ እንዲሻሻል፣ ምርታማነት እንዲጨምር፣ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የህግ ዋስትና እንዲያገኙ፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚያስችሉ ሀሳቦችን ለማቅረብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋት መስራት ከምሁራን እንደሚጠበቅ አቶ እስቅያስ አሳስበዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ መሰል የውይይት መድረኮቸን እንዳዘጋጀ አስታውሰው ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው በማንኛውም ሁኔታ በህዝባችን ህይወትና ኑሮ ላይ መሻሻል ሊያመጣ የሚችል በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ከምሁራን ቢቀርብለት አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከንቲባው አማካሪ አቶ ብሩክ ግዛው የኢህአዲግ ውህደት አግላይ የነበረውና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን በፖለቲካ ውስጥ አነስተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርግ የነበረውን ስርዓት አስቀርቶ ንቁ ተሳታፊና በውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ሚናቸውን የሚያጎላ ነው ብለዋል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ትክክለኛ የሆነ የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዲኖር የሚታገል እንደሆነ የገለፁት አቶ ብሩክ ይህን የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለማስፈን እየሰራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት በማረጋገጥና ብዝሃነትን በመጠበቅ የፌዴራል ሥርዓቱን ማጠናከር ይቻላል ያሉት አቶ ብሩክ የጋራ የሆኑ ብዙ ጉዳዮች አሉንና የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ አጠንክረን በመስራት ለፌዴራል ሥርዓቱ መጠንከር አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡ የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ብልፅግና ፓርቲ ያነገበው ዓላማ መሆኑን በመግለፅ የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከታከለበት ይህን ዓላማ ለማሳካት እንደሚቻል በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በውይይት መድረኩ ላይ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ቀደም ሲል የምሁራን በአገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ውስንነት እንደነበረው በመግለፅ አሁን ይህ የውይይት መድረክ ምሁራንን አሳታፊ መሆኑን አድንቀዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ቀጣይነት እንዲኖረው በመጠቆም፡፡ ልዩነታችን ውበት አንድነታችን ጥንካሬያችን ነውና ለሃሳብ ልዕልና ዋጋ በመስጠት በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት በአንድነታችን ውስጥ ያለውን ጥንካሬ ለማጉላት መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማህበራዊ መሰረታችንን አደጋ ላይ ጥሎታል ያሉት ተሳታፊዎቹ አሁን ግን ውህደቱ ይህን በቂ ትኩረት ያልተሰጠውን የህብረተሰቡን ማህበራዊ መሰረት በቂ ትኩረት በመስጠት ከአደጋ እንደሚጠብቀው ገልፀዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በሚዲያዎች ሀሳብን በመግለጽና በጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተዋጽኦ በማድረግ ምሁራን ወደ ብልጽግና በሚደረገው ጉዞ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ ምሁራን በአስተዳደሩ በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም የላቀ አስተዋጽኦም እንዲያበረክቱ የምሁራን ምክር ቤት ቢቋቋም መልካም መሆኑንም ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡ ምሁራን በእውቀት ላይና በመርህ ላይ በመመስረት፣ ችግሮችን የማሳየትና የችግሮቹ የመፍትሔ አካል ሆኖ ለመፍትሔው መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ተሳታፊዎቹ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በሚጠቅምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሀሳብ ግብዓት በመስጠት አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን በአግባቡ በመጠቀምም ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ተብሏል፡፡ እንደ ጋና፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ያሉ አገራት በብሔር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ ከመመስረትና ከመገንባት ይልቅ አገራዊ ፓርቲ በመገንባት ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት ችለዋል ያሉት ተሳታፊዎቹ ብልፅግና ፓርቲም አገራዊ ርዕይ ይዞ መነሳቱ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ከምሁራን በተነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ላይ በመድረኩ በተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከንቲባው አማካሪ አቶ ብሩክ ግዛው እና በመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ምላሽ ተሰጥቶባቸው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡