ለመጪው ትውልድ ምቹ ድሬዳዋን ለማስረከብ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በጋራ ልንሰራ ይገባል ተባለ፡፡

0
47

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ለአስተዳደሩ ነዋሪ የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ግንዛቤ ለመጨመር ያለመ አስተዳደራዊ ኮንፈረንስ አካሂዷል፡፡ ‹‹ያልተገራ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም የመጪውን ትውልድ ህልውና የሚጋፋ ተግባር ነው››በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ኮንፍረንስ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ እንደተናገሩት ድሬዳዋ በተፈጥሮ አደጋ መጠቃቷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን በማስታወስ፡፡ድሬዳዋ የበረሀዋ ንግስት ተብላ አረንጓዴ የነበረች ቢትሆንም አሁን ከሚታየው ሁኔታ ችግር ውስጥ እየገባች መሆኗ ሊያሳስበን ይገባል ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ በአካባቢ ልማት ላይ የመስራት ባህል ተዳክሟል ያሉት አፈ ጉባኤዋ በተለይ ፋብሪካዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ፈጡም አክለውም ለልጆቻችን ምቹ ድሬዳዋን ለማስረከብ በጋራ ልንሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የአስተዳደሩ የአካባቢ የደን አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ አብዶ አህመድ የድሬዳዋ አሁናዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው በመናገር፡፡ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም በከርሰ ምድርና በገፀ ምድር ሀብት የበለጸገች ነበረች ዛሬ ያላት ሀብቷ ተመዝብሯ ብለዋል፡፡ ድሬዳዋ የምትታወቀው በግንባታ ማእድናት እና በከርሰ ምድር ውሀ እንደነበር በመግለጽ በአሁን ሰዓት የተፈጥሮ ሀብቶቿ ተመናምኗል ብለዋል ፡፡ እንደ አቶ አብዶ ገለጻ ባለስልጣኑ የውሃና የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ያሳተፉ የልማት ስራዎችን ለመስራት ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ ተቋም ስራ ባለመሆኑ የህልውና ጉዳይ የሆነውን ይህንን ስራ ሁሉም ዜጎች በርብርብ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የባለስልጣኑ ኃላፊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በኮንፍረንሱ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላቶች የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበዋል፡፡

በትዕግስት ቶሎሳ