‹‹ህግ የማስከበር ስራ ላይ ባለስልጣን መ/ቤቱና ግብር ከፋዩ ተቀራርቦ መስራት ይጠበቅበታል›› አቶ ካሊድ መሀመድ የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን የሉካንዳ ንግድ ዘርፍ ግብር አወሳሰን እና አሰባሰብ ሥርዓትን ለመወሰን አዲስ በወጣው የአፈፃፀም መመሪያ ማሻሻያ ላይ ከግብር ከፋዮች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

0
127

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀደም ብሎ በስራ ላይ የነበረውን መመሪያ ቁጥር 8/2009 ያሉበትን ክፍተቶች በማጥናት በመመሪያ ቁጥር 18/2011 ማሻሻሉንም አስታውቋል፡፡ ይህ የሉካንዳ ንግድ ዘርፍ ግብር አወሳሰን እና አሰባሰብ ሥርዓትን ለመወሰን የተሻሻለው አዲሱ መመሪያ በግብር ሰብሳቢው ተቋምና በግብር ከፋዩ ህብረተሰብ መካከል ቀደም ብሎ ለአሰራር የሚያስቸግሩ አንቀፆችን በመለየት ማስተካከል የተቻለ ሲሆን ይህም የነበሩትን የአሰራር ችግሮች እንደሚቀርፍ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ ስለ ሽያጭ

መመዝገቢያ መሳሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ስብሰባውን የመሩት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ መሀመድ ህግ የማስከበር ስራ ላይ ባለስልጣን መ/ቤቱና ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ተቀራርቦ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ህግን ማስከበርም ሆነ ማክበር ደረሰኝ ከመቁረጥ ይጀምራል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ደረሰኝ ያለመቁረጥ ወንጀል መሆኑንም አውቆ በአግባቡ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የግብር ከፋዬች ትምህርትና ሥልጠና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሮክተሬት ዳሬክተር አቶ ሙስጠፌ ሙሴ በበኩላቸው ከግብር ከፋዬች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ላይ እንደገለፁት ግብር መክፈል የዜግነት የውዴታ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መብት መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ግዴታንም መወጣት ተገቢ መሆኑን አውቆ ሁሉም ግብር ከፋይ ግዴታውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ በመጨረሻ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሪፎርም ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን አጭር ጊዜ የግብር አሰባሰብና አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ ሀገር አቀፍ የሆነ የተቀናጀ የመንግስት የታክስ አስተዳደር ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንገኛለን ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይም የዚህ አይነት የታክስ ንቅናቄ ስራዎች የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል፡፡