የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት ይሻል ተባለ

0
63

አቶ ብሩክ አያሌው በድሬዳዋ አዲሱ 2ተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት የባዮሎጂ ቤተ- ሙከራ ቴክኒሺያን ነው፡፡ መምህሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውድድር ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡ በውድድሩም በኢንጅነሪንግ እና በማቲማቲክስ የፈጠራ ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆነ የፈጠራ ውጤት ማለትም ሽፈራውና ኪኒን ዛፍን ጨምሮ ከተለያዩ እጽዋት የሳሙና ውጤቶችን በማዘጋጀት ይዞ በመቅረብ 1ኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

 

አቶ ብሩክ ምንም እንኳን በውድድሩ ባገኘው ውጤት ድሬዳዋን ማስጠራት ቢችልም ከአስተዳደሩ እስካሁን የማበረታቻ እውቅናን እንዳላገኘ ይናገራል፡፡

የፈጠራ ባለሙያዎችን በየደረጃ ከማሳደግ ፤ ለከፍተኛ ደረጃ ከማብቃት አንጻር ይህ ነው የሚባል ስራ እንደማይከናወን መታዘቡን የግሉን አስተያይትም ሰጥቷል፡፡

እንደ አስተዳደር የከንቲባው ጽ/ቤት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት በዘርፉ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ዋነኛ ተልዕኮ አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የዳይሮክቴሬቱ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሀሩን አብዱረህማን የፈጠራ ባለሞያው አቶ ብሩክ አያሌው ያነሱት ችግርን ጨምሮ በዘርፉ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ በመንግስት የሚሰጠው ትኩረት እና ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ምንም እንኳን ዳይሬክቶሬቱ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም እስካሁን ለት/ቤቶች የሳይንስና ማቲማቲክስ ክበባት የፈጠራ አቅም ለመፍጠር የተሻለ መሆኑን አቶ ሀሩን ያስረዳሉ፡፡በከፍተኛ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ የፈጠራ ባለሙያዎች የመስሪያ ቦታ ለማመቻቸት ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የፈጠራ ባለሙያዎች በተለያዩ አገር አቀፍ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ለማስቻል ጥረት እንደሚደረግ አቶ ሀሩን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ዘላቂ የሆነ አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ ከ14 በላይ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የኢኖቬሽን ም/ቤት ይቋቋማል፡፡ ከአደረጃጀት ረገድም ከዳይሮክቶሬት ወደ ጽ/ቤት ለማሳደግ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን እነዚህና ሌሎች ተግባራት ሲከናወኑ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዝ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ አቶ ሀሩን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ባሳለፍነው ቅዳሜ ህዳር 27 በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ያሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡