ከኋላ ታሪካችን ዛሬን አንጻፍ

0
173

ታሪክ በታሪክነቱ የራሱ ሁለት ዋና ዋና  ገጽታዎች አሉት፡፡ በእኛም ሆነ በሌሎች እይታና ባመጡት ውጤት ሲገመገሙ  ጥቁር ጠባሳ ጥለው ያለፉ እንዲሁም ለማስታወስ እንኳን የሚከብዱ ታሪኮችን በመጥፎ ገጸታቸው የምናውቃቸው ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ታሪኮችን መለስ ብሎ ለአፍታ ማስታወሱ ስህተትን መድግም ለማይፈልግ አስተዋይ ሰው ትልቅ ፋይዳ አላቸው፡፡ ታሪኮቹ እንዳይደገሙ ለራሱም ግንዛቤ በመውሰድ ለሌላወም በማስገንዘብ በሀገርና በወገን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ገና ከጅምሩ ማስቀረት ይችላል፡፡

ሌላው የታሪክ ገጽታ በእኛም ሆነ በሌሎች እይታና ባመጡት ውጤት ስንፈትሻቸው በሀገር ገጽታ ላይ ሌላ ተጨማሪ በጎ ገጽታ የሚጨምሩ እና ትውልድ እየተቀባበለ የሚዘክራቸውን ታሪኮች በበጎ የታሪክ ገጽታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ይህንን ከሚመስሉ ታሪኮች ለስኬታቸው ቁልፉ ምን እንደሆነ በማጥናት እና አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተሸለ ታሪክ ለመስራት ብርታትን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ሁልጊዜ እየዘከርናቸው የእኛን ሌላ  አኩሪና በጎ ታሪክ ሳንሠራ እንኖራለን ማለት አይደለም፡፡

በጎም ይሁን መጥፎ የትላንትና ታሪክ ላይ ከሚገባው በላይ በማተኮር ጊዜን፣ጉልበትን እና ገንዘብን ማባከን ተገቢ አይደለም፡፡ ካሰለፍነው ታሪካችን መማር ያለብንን ቶሎ ተምረን ነገን የተሸለ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በትላንትና ታሪክ ብቻ እየተኩራሩ በመኖር ለውጥን ማምጣትና ሀገር መገንባት አይቻልም፡፡ ዛሬ በእጃችን ነው፤ ነገ ደግሞ የራሱን አዲስ አማራጭና ዕድል ይዞ ይመጣል፡፡

ትላንት በታሪካችን የነበረን የእርስ በእርስ መስተጋብርና ግንኙነት ጥሩ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ አንዳችን ለሌላችን ስናውቀውም ሳናውቀውም ጥሩ ላንሆን እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ የአንዲት ሀገር ዜጎችና የአንድ እናት ልጆች ነን፡፡ ለምንለያይባቸው ጉዳዮች ይልቅ አንድ የምንሆንባቸው ጉዳዮች ይበልጣሉ፡፡ ለዚህ ነው ስንደመር አንድ እንሆናለን የሚባለው፡፡

በትላንቱ መጥፎ ታሪካችን ህሊናችን እንዳይቆሽሽና እኛም ሳናውቀው የዚያ መጥፎ ታሪክ አካል እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ከትላንትናው ታሪካች እየወሰድን የዛሬውን ብሎም የነገውን ታሪካችንን መጻፍ አይገባም፡፡ ሁሌም አዲስ ነገር አለ፡፡

   የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       30/02/2011ዓ.ም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here