የተሳሳቱ መረጃዎች ስርጭት ለድሬደዋ ሰላም ማጣት መንስኤ እንደነበር ተገለጸ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት 43ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡

0
109

ባሳለፍነው ሳምንት 2ኛ የስራ ዘመን 43ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደው የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት በአስተዳደሩ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡ በጉባኤው ላይ የወቅቱን ጸጥታ ጉዳይ ሪፖርት ያቀረቡት የፍትህ ጸጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የሆኑት የተከበሩ አቶ ሙሳ ጠሃ ናቸው፡፡ የምክር ቤቱ ህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ግብረ መልስ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ውሎው የንግድ ኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንትና የግብርና ውሀ ፣ ማዕድን ኢነርጂ ቢሮን ሪፖርት በቢሮ ኃላፊዎች በኩል ቀርቦ ያደመጠ ሲሆን የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች እንዲሁም የግብርናና ተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ግብረ መልስም ለምክር ቤቱ አባላት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ የምክር ቤቱ አባላት በተለይም ከጋዜጠኞች ስነ ምግባር ጋር እና ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ ባለ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በመጨረሻም ረቂቅ ደንቡ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

 

በተለያዩ ጊዜያት በማህበራዊ ድህረ ገጾችም ሆነ በተወሰኑ ግሩፖች የሚነዙ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳቢያ የአስተዳደሩ ነዋሪ ሰላሙን እንዲያጣ አይነተኛ ሚና መጫወቱን የተናገሩት የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ አመራሩ ይሄንን እታች ድረስ ወርዶ በማጣራትና ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ በመስጠት ህዝቡን የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር የድሬደዋ አስተዳደር ም/ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው ህጋዊ ባልሆነ አደረጃጀት የሚመራ አካል እንዳለ ገልጸው፤ የህግና የእርቅ ጉዳይ ደግሞ እየተቀላቀለ ህግ በአግባቡ እንዳይተገበር ምክንያት እየሆነ የመጣበት ሁኔታም ስላለ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ነጣጥሎ ማየት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ 1 መቶ 10 ሰዎች መኖራቸው በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን በማስረጃ በተደገፈ ምርመራ 51 ተጠርጣሪዎች ተለይተው በልዩ ሁኔታ እየተመረመሩ እንደሚገኙና በቀጣይም የምርመራው ሂደቱን ውጤት በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡