ወጣቶች የድሬዳዋን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

0
96

የድሬዳዋ አስተዳደር ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከሁሉም የከተማ ቀበሌዎች የወጣት ሊግ ስራ አስፈጻሚዎች እና ተፅእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ወጣቶች ጋር በከተማዋ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እና የቀጣይ  መፍትሔዎቻቸው ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

 

በውይይቱም ግጭትን መቆጣጠር እና ስለድሬዳዋ እሴቶች የሚዳስስ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በቀረበው ሰነድ ላይ ወጣቶች ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የአብሮነት፣ የመቻቻል እና የፍቅር ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ ወደ ቀድሞው የምትታወቅበት ስሟ ለመመለስ እኛ ወጣቶች ከስሜታዊነት በፀዳና ውይይትን ባስቀደም የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት ይገባናልም ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ አና ኡመር ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቱ ትኩስ ሀይል በመሆኑ ምክንያታዊ ጠያቂና የሌሎችን አጀንዳ አስፈጻሚ ከመሆን ተቆጥቦ የጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ መሪ ተዋንያን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

 ባለፉት 3 ዓመታት በነበሩ ችግሮች ሰለባ እየሆነ ያለው ወጣቱ ነው፣ በቀጣይ ወጣቱ ሰላመምን አስጠብቆ  ህብረ-ብሔራዊነቱን ጠብቆ በፍቅርና በመተባበር የምንኖርባት ድሬዳዋን መመለስ አለብን ሲል የድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶች ሊግ ሊቀ መንበር ወጣት ፍራኦል ቡልቻ ተናግሯል፡፡

ወጣት ፍራኦል  አክሎም ተመርቀው ለተቀመጡ ወጣቶች በአስተዳደሩ ባሉት ክፍት የስራ ቦታዎች የታሳቢ ቅጥር እንዲፈጸም የወጣት ሊግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለፅ ሌሎች በአስተዳደሩ ያሉ የስራ አጥ ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለአስተዳደሩ ካቢኔ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም መሰል የውይይት መድረኮችን ከቀበሌ እስከ መንደር ድረስ ወርደው ወጣቱን ለማወያየት  ማቀዳቸውንም ወጣት ፍራኦል ገልፃል፡፡