‹‹አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን እናረጋግጣለን›› ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን የማረጋገጡ ሥራ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

0
93

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን የማረጋገጡ ሥራ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በከተማ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ህዝባዊ ውይይቶች ማድረግና ህዝባዊ አደረጃጀቶችን የመፍጠር ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ህዝቡን በጥልቀትና በስፋት አወያይቶ የመፍትሄው አካል ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልፁ ለአንድ ወር ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው 05 እና 06 ቀበሌዎች ላለፉት ሶስት ቀናት ችግር አለመፈጠሩ ማሳያ ይሆናል ብለዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የተማሩ ወጣቶች በስፋት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አስተዳደሩ ያሉትን የሥራ ቀዳዳዎች ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመንግስት መዋቅሮች፤በባህልና ቱሪዝም፣በስራ ዕድል ፈጠራ ፤ በኢንዱስትሪ ፓርክ ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ በሌሎችም ዘርፎች ወጣቶችን ተጠቃሚ ይደረጋል ብለዋል፡፡
‹‹በሀገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ የሥራ እጥ ከተማ የመሆኗ መንስኤ የስደተኞች በር መሆኗ ጭምር ነው፤ የሥራ እጥ ቁጥር 24.5 በመቶ ነው፤ ይህን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ለሰላም ትልቅ ዋጋ አለው›› ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ኢንዱስትሪና ኢንቨስትምንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ከሁሉም ቀበሌዎቾ ነዋሪዎች ተወካዮች ፣ ከሐይማኖት አባቶችነ፣ከሐገር ሽማግሌዎች ፣ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ ነዋሪዎች መንግስት የህዝቡን የመኖር መብት ፤ከስጋትና ከፍርሃት ነፃ የማድረግ ኃላፊነቱን በመፍጥነት እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትን ከቃል በዘለለ በተግባር እንዲያረጋግጥና ያለ ስጋት የሚኖሩበት ሰላም እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ለሰላም መደፍረስ አንዳንድ ፅንፍ የረገጠ መረጃ የሚያስተላፉና በህዝቦች መሃል ግጭት የሚፈጥሩ ሚዲያዎች በመኖራቸው በነዚህ ላይ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ በአስተዳደሩ ሥር የሰደደውን የሥራ እጥነት መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ለብሔራቸው ብቻ እየወገኑ ያሉ አመራሮችን ተጠያቂ መደረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ለግጭቱ መስፋፋት ከሌሎች ስፍራ ተደራጅተው ወደ ከተማዋ በመግባት የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የማዳግም እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ አክለው እንደተናገሩት ከፀጥታ አካላት ጋር ህብረት በመፍጠር ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ለህግ አሳልፎ ከመስጠት ጀምሮ ለከተማቸው ሰላምና ፀጥታ መከበር ኃላፊነታቸውንም እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡