አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የህግ የበላይነት የማስከበር እርምጃው አጠናክሮ ቀጥሏል።

0
99

ሰሞኑን በተፈጠረው ረብሻና ሁከት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 110 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ላለፉት ሶስት ቀናት በድሬዳዋ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል የተባሉ 110 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የድሬዳዋ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል፡፡

በአስተዳደሩ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። በተከሰተው ረብሻና ብጥብጥ ዜጎች ህይወታቸው አልፏል፤ በርካቶች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ሃብትና ንብረት ተቃጥሏል፤ ተዘርፏልም፡፡

ሁከትና ብጥብጡ ያስከተለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ፖሊስን ዋቢ በማድረግ መረጃ የሰጡት የድሬዳዋ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደተናገሩት፤ በተፈጠረው ግጭት የሰባት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

 

ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ባልታወቁ በርካታ ዜጎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንና በህክምና ላይ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡ በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪም በ25 ቤቶች ላይ ከፍተኛ ዘረፋ የተፈፀመ ሲሆን 4ቱ ቤቶች በእሳት መውደማቸው ታውቋል፡፡

በዘረፋው ተግባር ላይ ከሌላ አካባቢ የመጡና ችግሩን ያባባሱ በቡድን የተደራጁ ሰዎች ጭምር መሳተፋቸውን አቶ እስቅያስ የገለፁ ሲሆን ችግሩ እንዲስፋፋና በከተማዋ ላይ መጠነ ሰፊ ቀውስ ለመፍጠር ብሔር ተኮር ጥቃቶች መፈፀማቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በኃይማኖት ተቋማት ችግር ለመፍጠርና ግጭቱ የኃይማኖት መልክ እንዲይዝ የተደረገው ጥረት በፀጥታ አካላትና በሰላም ወዳዱ ነዋሪ ደጀንነት ሊከሽፍ ችሏል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ እስቅያስ ገለፃ ፖሊስ ድብቅ አጀንዳ አንግበው የብሔርና የኃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበር ብሎ የጠረጠራቸውን 110 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ ይገኛል፡፡ ተጠርሪዎችንም በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።