ባለፉት 3 ወራት ብቻ ከ284 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

0
110

የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ አመት ለመሰብሰብ ካቀደው 345 ሚሊየን 270 ሺህ ብር በላይ ገቢ ከ284 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ የእቅዱን 82 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል፡፡

 

የባለስልጣኑ ዳይሬክተር አቶ ካሊድ መሀመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ገቢው ካምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ24 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

ለእቅዱ መሳካት በበጀት አመቱ መግቢያ የተከናወነው የንቅናቄ እና እውቅና መድረኮች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋሙም ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በመፈተሽ የወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲሁም አቶ ካሊድ ጠቁመዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተያዘው የመጀመሪያ ሩብ አመት ለመሰብሰብ ካቀዱት 345 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ከ284 ሚሊየን ብር በላይ በማስገባት የዕቅዱን 82 በመቶ አሳክቻለሁ ብሏል፡፡

የግብር ከፋዮችን የተጨማሪ እሴት ታክስ ሪፖርት በማጣራት በሉካንዳ ቤቶች ላይ የሚወሰነውን ግብር ፍትሐዊ ለማድረግ ቀደም ሲል የነበረውን መመሪያ ማሻሻል እና መሰል እርምጃዎች በውጤቱ ተጠቃሽ ናቸው ነው ያሉት፡፡

ሌላው ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በሚጠበቀው መጠን አለመሆን የነበሩ የጸጥታ መደፍረሶችና መሰል ችግሮች ግቡን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ተግዳሮት ቢሆኑም በበጀት አመቱ ለማሳካት የታቀደውን የ1.5 ቢሊየን ብር ገቢ ለማሳካት ችግሮቹን በመቅረፍ በቀጣይ ሰፊ ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል፡፡ ግብር ከፋዩም በተለይ የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮችም ወሩ የግብር መክፈያ ወቅት መሆኑን በመረዳት ግብራቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉም አቶ ካሊድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡