ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሪፈራል ሆስፒታሉን ሙሉ ለሙሉ ተረከበ

0
406
  • ሆስፒታሉ በአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ በተደረገላቸው አካላት ተጎብኝቷል::

     በግንባታው መዘግየት በርካታ አመታትን ያስቆጠረው የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል የአስተዳደሩ ካቢኔ በጥር 15 ቀን 2010 ዓ/ም ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ሙሉ ለሙሉ አሁን ባለበት ሁኔታ ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡

     ባሳለፍነው ሳምንት በከንቲባ ፅ/ቤት በተደረገው የሪፈራል ሆስፒታሉ ርክክብ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ስነ ስርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መሀመድ አህመድ እንደተናገሩት ግንባታው መዘግየቱ ህብረተሰቡ ከዘርፉ ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት ማግኘት እንዳይችል ማድረጉ በአመራሩ ዘንድ ታምኖበታል፡፡ ስለሆነም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቀሪውን ግንባታ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ወደ ስራ በመግባት ለነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ ጥሩ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ታምኖበት እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለመማር ማስተማር ሂደቱም ይረዳዋል የሚለውን ሃሳብ ታሳቢ በማድረግ ጭምር የአስተዳደሩ ካቢኔ አምኖበት የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ለዩኒቨርሲቲው ተሰጥቷል፡፡

     በዋናው ኮንትራክተር ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ለአንድ አመት ያህል ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የነበረው ይህ ሪፈራል ሆስፒታል አሁን 62 በመቶ ስራው መጠናቀቁ ነው የተገለፀው፡፡ ሆስፒታሉ በአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ በተደረገላቸው አካላት በተጎበኘበት ወቅት እንደተገለፀው ከተያዘለት የ3 መቶ 34 ሚሊዮን ብር በጀት ውስጥ እስካሁን 2 መቶ 50 ሚሊየን ብር ወጪ ሆኖበታል፡፡ የግንባታ ስራው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የተጠናቀቀው ሆስፒታሉ ቀሪ የኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታና የማጠናቀቂያ ስራዎች ይቀሩታል፡፡ የሪፈራል ሆስፒታሉ  ባለቤት የሆነው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው ግንባታውን አሁንም በፍጥነት ለማጠናቀቅ በዋናነት የህዝቡን ታላቅ ርብርብ እንደሚጠይቅ አልሸሸጉም፡፡

 

     ዩኒቨርሲቲው በያዘው እቅድ መሠረት በ1 አመት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቅቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው ዶ/ር ያሬድ ያስታወቁት፡፡

     አመራሮቹ በጉብኝታቸው ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ህንፃ እንዲሁም  በ10 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን ያሣረፈውና 95 በመቶ ግንባታውን ያጠናቀቀው 6 ሺ  ታራሚዎችን መያዝ የሚችል አቅም ያለውን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ግንባታም ጎብኝተዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱም በ2012 ስራ ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡