የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ ወረርሽኝ እንድንከላከል ጥሪ ቀረበ  በቺኩን ጉንያ የተጠቁ ሠዎች ቁጥር ወደ 7ሺ 258 አሻቅቧል፡፡

0
267

ባሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 15 2011 ዓ/ም ድረስ ብቻ በቺኩን ጉንያ ቫይረስ ተይዘው ወደ ሆስፒታል የመጡ ሰዎች ቁጥር 7 ሺ 258 መድረሱን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ፉአድ ከድር አስታወቁ፡፡ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ንፅህና በመጠበቅ ወረርሽኝን እንዲከላከል ጥሪ ቀርቧል፡፡

     የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ወረርሽኝ ለመከላከል የህዝቡ ርብርብ ወሳኝነት እንዳለው ነው ያስታወቁት፡፡ በሽታው ከቀን ወደ ቀን የመዛመት አቅሙ እየጨመረ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ያልሸሸጉት ኃላፊዎቹ በዋናነት ነዋሪው አካባቢውን በማጽዳትና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማዳረቅ በሽታውን እንዲከላከል መክረዋል፡፡

     መንግስት በሽታው በታየባቸው አካባቢዎች የኬሚካል ርጭት በማድረግ፣ በማህበራት ዲሾችን በማፅዳት እንዲሁም ስለበሽታው ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎችን ከፌደራል መንግስት እገዛ እንዲያደርጉ ወደ አስተዳደሩ በማስመጣት ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ መሆኑን የተናገሩት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞችንም ጭምር ስለ በሽታው ግንዛቤ በማስጨበጥ በአስተዳደሩ ያሉ ቆሻሻ ስፍራዎችን በጋራ በማጽዳት በሽታን ቀድመው እንዲከላከሉ የማድረግ ስራ መከናወኑንም ገልፀዋል፡፡

 

     በሽታው በራሱ ገዳይ ባለመሆኑ እስካሁን በቺኩን ጉንያ ቫይረስ የሞተ ሰው ባይኖርም ከተጓዳኝ በሽታዎች ጋር ሲሆን ግን ሌላውን በሽታ በማባባስ ለሞት ሊያደርስ እንደሚችል ዶ/ር ፉአድ ከድር ተናግረዋል፡፡ በሽታውን ለመቆጣጠር ቢሮው ከውሃ ልማት፣ ከፅዳትና ውበት እንዲሁም ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በተቋማቱ እንቅስቃሴ ብቻ አመርቂ ውጤት ስለማያገኝ ማህበረሰቡም የአካባቢውን ንፅህና በመጠበቅ አጎበር በመጠቀምና የተጠራቀሙ የዝናብ ውሃዎችን በማፍሰስ ትንኟ እንዳትራባ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡