“መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻሉ ችግሩ ተባብሷል” ዶ/ር ደራራ ሁቃ

0
231
  • 1 መቶ 3 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገብቷል፡፡
  • 1 መቶ 20 ሺ ካሬ ቦታ ለመምህራን ተዘጋጅቷል፡፡

     በተለያዩ የአስተዳደሩ አካባቢዎች ህገ ወጥ የመሬት ወረራዎች ለመበራከታቸው ምክንያት ከሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ መንግስት የህግ የበላይነትን በአግባቡ ማስከበር ባለመቻሉ እንደሆነ የድሬዳዋ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ደራራ ሁቃ ገለፁ፡፡ ኃላፊው ይህንን የተናገሩት ባሳለፍነው አመት ውስጥ ቢሮው ስለ አከናወናቸው ተግባራትና ስለ አጋጠሙት መሰናክሎች እንዲሁም በቀጣይ ሊሰራ ባቀዳቸው ስራዎች ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

     የቢሮው ኃላፊ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት በተለያዩ የመንግስት ተቋማት እንዲሁም በግለሰቦች ተይዘው ያለስራ የተቀመጡ 1 መቶ 3 ሄክታር መሬት ከባለይዞታዎቹ በመውሰድ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ አመትም እንዲሁ ጥናት ተደርጎባቸው የአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ ብቻ የሚጠባበቁ ቦታዎች አሉ፡፡ 2 መቶ 16 ሄክታር መሬትም አስተዳደሩ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት ለልማት ስራ ለማዋል መዘጋጀቱን  ኃላፊው ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

     ላለፉት 6 አመታት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ በቢሮው ላይ ሲነሳ የነበረው ችግር 38 የልማት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ታሳቢ በማድረግ የልማት ተነሺ ከሆኑ 1 ሺ 359 አርሶ አደሮች መካከል 23 ሄክታሩን መሬት ለ3 መቶ 40 አባወራዎች ካርታ በመስጠት ችግሩን ያቃለለበት ሁኔታ እንዳለ የተናገሩት ኃላፊው በሂደት ሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል፡፡

     በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ ለሚያስተምሩ 1ሺ 200 የሚሆኑ መምህራን 1 መቶ 20 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ዝግጁ መደረጉን የገለፁት ዶ/ር ደራራ በ2012 በጀት አመት መምህራኑ በማህበር በመደራጀት ቦታውን መረከብ የሚችሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

     በተጨማሪም ባሳለፍነው አመት ብቻ 2.8 ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል ላስመዘገቡ 54 ኢንቨስተሮች 1 መቶ 93 ሄክታር መሬት መስጠቱን የተናገሩት ኃላፊው መሬቱም 1 መቶ 34 ሄክታሩ ለሪል ስቴት መስሪያ፣ 35 ሄክታሩ ለማኑፋክቸሪንግ (አምራች) ዘርፍ እንዲሁም 24 ሄክታር ለአገልግሎት ዘርፍ የሚውል ነው ብለዋል፡፡

    ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት ለሚነሱበት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዋናው በውስጥ ያሉ ሰራተኖች የስነ ምግባርና የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ነው ይህን እንዴት ትመለከቱታላችሁ? ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተነሣው ጥያቄ አቶ ደራራ ሲመልሱ በተለያዩ ጊዜያት የማይገባ ጥቅምን ለማግኘት ሲባል አድሎአዊ ማስረጃ በመላክ የፍርድ ሂደትን እስከማዛባት ድረስ የሚደርሱ ባለሞያዎችን በቢሮ ደረጃም ሆነ በህግም የሚጠየቁበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም አመራሩም ጉዳዮቹን በመፈተሸና በማየት ኃላፊነት የሚወስድበት ሁኔታ መኖሩን በመጠቆም ሁሉንም በሂደት እያጣራ እርምጃ ለመውሰድ ቢሮው ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡