የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ለአዲሱ በጀት ዓመት ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ አጸደቀ

0
72

የአስተዳደሩ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ ከ2 ቢሊዮን 8 ሚሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ በጀት
በማጽደቅ እና ወ/ሮ ከሪማ አሊን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ በማድረግ ተጠናቅቋል፡፡ የህግ
የበላይነትን በማረጋገጥ የሥራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ
እንደሚሰራም የድሬዳዋ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
ለሁለት ቀናት የተካሄደው 2ተኛ የሥራ ዘመን 42ኛው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ዓመታዊ
ጉባኤ ሲጠናቀቅ የድሬዳዋ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ እንደተናገሩት በአዲሱ በጀት
ዓመት የገጠርና የከተማ ሥር የሰደደ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ
ለመፍታት ይሰራል፡፡
የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ጉዳይ ትኩረት
ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ በተለይ በአስተዳደሩ የሚስተዋለውን የሥራ አጥነት ለመቀነስ የተቀናጀ ሥራ
በመስራት ለ18 ሺ ሰዎች ይበልጥኑ ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ነው የተገለፀው፡፡
በገጠርና በከተማ በልማትና በአገልግሎት አሰጣጥ ከህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚነሱ ችግሮችን
የመፍታት ጉዳይም በአዲሱ ዓመት ትኩረት ማግኘቱን ያስታወቁት አቶ ሱልጣን፤ የተወጠኑትን ዕቅዶች
በትክክል ለመከወን 2 ቢሊዮን 834 ሚሊዮን 440 ሺ ብር ረቂቅ በጀት ለአዲሱ በጀት ዓመት መያዙን
ተናግረዋል ፡፡
እንደ አቶ ሱልጣን ገለፃ ከተያዘው በጀት ውስጥ 46.2 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ
የሚውል ነው፡፡ የበጀቱ ምንጭ ከአስተዳደሩ ከሚሰበሰብ ገቢና ከፌደራል መንግስት የሚገኝ መሆኑን
ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ረቂቅ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ የተቀመጡት የትኩረት
መስኮች ጥሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ ኢብራሂም መሐመድ እየጨመረ ያለው የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን
ለመመለስ ለካፒታል ፕሮጀክት ማስፋፊያ የተያዘው በጀት ከፍ ማለት ነበረበት ብለዋል፡፡
አቶ ሱልጣን አልይ ጥያቄው ትክክል መሆኑን ገልፀው ዘንድሮ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ይበልጥ
በማዘመን ምጣኔ ሃብቱ የሚያመነጨውን ያህል ሃብት እየተሰበሰብ ሲመጣ የካፒታል ፕሮጀክቶች በጀት
ይመጣጠናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የምክር ቤቱ አባላት የዘንድሮ በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን 834 ሚሊዮን 440 ሺ
ብር ረቂቅ በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቀውታል፡፡ ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ውሎው ተጠሪነታቸው ለምክር
ቤት የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡
ከበጀቱ በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላት ወ/ሮ ከሪማ አሊን የአስተዳደሩ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ
ቢሮ ኃላፊ ሹመት በመስጠት ዓመታዊ ጉባኤውን አጠናቋል፡፡