“የድሬዳዋን የፍቅርና የአንድነት መግለጫ እሴቶች ለመመለስ መረባረብ ይገባል” የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ

0
538

ለሀገር አርአያ የሆነውን የድሬዳዋን የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት መገለጫ እሴቶች ለመመለስና
ሀገር አቀፉን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል
ከንቲባ አህመድ መሐመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡
‹‹አንድ ዕድል ለሰላም›› በሚል መሪ ሃሳብ በተኪያሄደው የዛፍ ጥላ ሥር የእርቅ ውይይት ላይ
ሀገር አቀፍ ታላቅ ስብዕና የተላበሱ የሀገሪቱ የኪነ ጥበብና የዘርፈ ብዙ ሙያተኞች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ እንደተናገሩት
ድሬዳዋ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች በፍቅርና በአንድነት የፍቅር ዋርካ ናት፡፡
ይህ ለሀገር አርአያ የሆነውን ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለመሸርሸር የሚደረገው ጥረት ቦታ እንደሌለው
በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
በመሆኑንም የድሬዳዋ አርአያዊ አንድነትን ለመጠበቅና በትውልድ ውስጥ የትላንቱን ታላቅ የህብረት
ስብዕና ለመመለስ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡
በተለይ በዛፍ ጥላ ሥር የተጀመረውን የእርቅና የውይይት ባህላዊ እሴት በማጎልበት የድሬዳዋን የፍቅር
መገለጫ እሴቶች ለመመለስ የተዋቀረው የአባቶች የሰላም ኮሜቴ ወሳኝ መሆኑን ነው ምክትል ከንቲባው
የገለጹት፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት እንደ የክቡር ዶ/ር አሊ መሐመድ ቢራ እና እንደ የክቡር ዶ/ር አሊ ሸቦ
ኮሚቴውን በማገዝ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሀገሪቱ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የሰላም አያያዝ በአስተማማኝ መንገድ እንዲጠበቅና እሷም
ሆነች ሌሎቹ ወገኖቿ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይህን ሃሳብ መፀነሷን የተነገረችው የ2019 የአለም
የማህበረሰብ አገልግሎት ሚስዝ ወርልድ አሻናፊና የድሬዳዋ ተወላጅ ፈቲሃ መሐመድ ናት፡፡
‹‹ዛሬ የድሬዳዋን ፍቅርና አንድነት ለመመለስ የተጀመረው ጥረት በቀጣይ በሌሎችም ለሀገሪቱ
ክፍሎች ይዳረሳል›› ብላለች፡፡
በዛፍ ጥላ ሥር በተኪያሄደው አገር በቀል የእርቅ ውይይት ላይ የተገኙት የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም
ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና ፍቅር ለመጠበቅ ባህላዊ
የሽምግልና እሴቶችን በሥራ ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ውስጥ ለሀገርና ለአለም የሚተርፍ ባህላዊ የሽምግልና እሴቶች
መኖራቸውን ተናግረው እነዚህን እሴቶች ተግባራዊ ማድረግ ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት
ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ለነዚህ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ትኩረት ተደርጎ የሀገሪቱ ሰላምና የህዝቦችን አንድነት
አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
‹‹በተለይ እነዚህን እሴቶች ለወጣቱ በማውረስ የሀገሪቱን ሰላም እና ዕድገት የሚጠብቅ የሰከነ
ትውልድ መፍጠር ላይ መረባረብ ይገባል›› ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፈው የክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራ የሚጣፍጠውንና ሁሉንም
አቃፊና ደጋፊ የሆነው የድሬዳዋን አንድነት፣ ሰላምና መተባበር እሴቶች ወደ ነበረበት ለመመለስ እሱም ሆነ
ሌሎች ወዳጆቹ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አረጋግጧል፡፡
‹‹ሃሳቡን ያመጣችውን ፈቲሃ መሐመድን አደንቃለሁ፤ እኛም በምንጓዝበት ቦታ ሁሉ ይህን
የድሬዳዋን ህብረት ለመመለስ ኃላፊነታችንን እንወጣለን›› ብሏል፡፡
በዛፍ ጥላ ስር ውይይት ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የሰላምና የእርቅ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ
የትነበርሽ ንጉሴ ድሬዳዋ የፍቅር አርማና የአንድነት መገለጫ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ድሬዳዋ ለሀገሪቱ ህዝብ ፍቅርና ሰላም የምትሰብክ የአፍሪካ ዱባይ እንድትሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ሁለቱም ኃይማኖቶች በተመሣሣይና በእኩል መንገድ የሚስተናገዱበት ከተማ መሆን አለበት ያሉት
ወ/ሮ የትነበርሽ ድሬ ግቡ እንጂ ውጡ የሌለባት ከተማ በመሆን አርአያነቷን ማሳየት እንዳለባት ገልፀዋል፡፡
‹‹አንድ ዕድል ለሰላም›› በሚል መሪ ሃሳብ በተኪያሄደው የዛፍ ጥላ ሥር ውይይት የተሳተፉት
በሀገሪቱና በአለም አቀፍ ደረጃ ዝና የተላበሱ ሙሁራን፤ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የድሬዳዋን ብሎም
የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት በአስተማማኝ መንገድ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ኃላፊነታቸውን
እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ መጨረሻ የተጀመረው የዛፍ ጥላ ሥር ውይይት የሚያስቀጥሉ፤ ለሚፈጠሩና ለተፈጠሩ
ግጭቶች በባህላዊ መንገድ ዕርቅ መፍጠር የሚችሉ ከሁሉም መስክ የተውጣጡ አባላት ያሉበት የአባቶች
የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ኮሚቴው የድሬዳዋ የፍቅርና አንድነት ወደነበረበት ለመመለስና የሀገሪቱን
ሰላም በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል፡፡
ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማት ተበርክቷል፡፡ ሲል የዘገበው
የኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅፈት ቤት ነው፡፡