የባከኑ የህዝብና የመንግስት ሃብቶችን ማስመለስና አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ተባለ

0
279

የባከኑ የመንግስትና የህዝብ ሃብቶችን ማስመለስና አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ላይ
ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡

ለገጠሩ ህዝብ ፍትህን ተደራሽ የማድረግ ሥራም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የተገለፀው፡፡
የአስተዳደሩ ምክር ቤት 42ተኛ ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ በአስተዳደሩ የዋና ኦዲተር ጽ/ቤት፤
የምክር ቤቱ ጽ/ቤት፤ የብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ፣ በአስተዳደሩ የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ
ቤቶች የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ ሱልጣን አልዪ እንደገለፁት፤ ለበርካታ ዓመታት በኦዲት ባለሙያዎች
ተበጥሮ፣ ተፈትሾና ተጣርቶ የተገኘን የሃብት ብክነትና ጥፋት ላይ እየተወሰደ የሚገኝ እርምጃ የለም፡፡
በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የባከነ የህዝብና የመንግስት ሃብት መመለስ አለበት፤
አጥፊዎችንም በህግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ለዚህ አሳሳቢ ችግር ፈጣን መፍትሄ
ለመስጠት ምክር ቤቱ ቁርጠኛ መሆን አለበትም ብለዋል፡፡
አቶ አብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የገጠሩ ህብረተሰብ ፍትህን ፍለጋ ለቀናት ከተማ እየመጣ
ሃብቱን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን እያባከነ በመሆኑ ለችግሩ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ
ገልፀዋል፡፡
በአዲስ በጀት ዓመቱ በአራቱ የገጠር ክላስተሮች ተዘዋዋሪ ችሎት ቢጀመር የህብረተሰቡን
መንገላታት በማስቀረት የፍትህ ተደራሽነትን ማሳካት ያስችላልም ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ማሞ የባከኑ የመንግስትና የህዝብን
ሃብት የማስመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ተደርጎ እየተሰራ ነው፤ አመራሩን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ የባከነው
ሃብት ከተመለሰ በኃላ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡
የኦዲት ግኝትን መነሻ በማድረግ 5 ተቋማት ተጠያቂ ተደርገው በጠቅላይ አቃቤ ህግ ምርምር
እየተደረገባቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብና የመንግስት ገንዘብም ከኮንትራክተሮች ማስመለስ መቻሉን ነው
አቶ ስንታየሁ የተናገሩት፡፡
ከነዚህ በተጨማሪ 19 ተቋማትና ኃላፊዎች በምርመራ ላይ መሆናቸውን ገልፀው፤ በምርመራ
ግኝት መሰረት የባከነ ሃብትና ንብረት ይመለሳል፤ ተጠያቂነትም ይከተላል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በሌብነት ተግባር የተሰማሩ
አካላት በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ከዳር ለማድረስ የተቀናጀ ርብርብ ይደረጋል ሆኖም ሥራው
ጥንቃቄና ማጥራት ስለሚፈልግ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል፡፡
እንደ አፈ-ጉባኤዋ ገለፃ ፍትህን ተደራሽ ማድረግና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራ በቀጣይ ልዩ
ትኩረት ተሰቷቸው ይሰራል፡፡ የፖሊስን፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን የማጠናከርና የዳኞችን ደህንነት

በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቁ ሂደት በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ አምና በድሬዳዋ የተከሰቱ
የፀጥታ ችግሮች ከዚህ በኃላ እንዳይደገሙም ይሰራል ብለዋል፡፡