በድሬዳዋ አስተዳደር የተከሰተውን የቺኩንጉንያ ወረርሽኝ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ

0
357

በድሬዳዋ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተውን የቺኩንጉንያ ወረርሽኝ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ
አስታውቋል።

የጤና ቢሮው በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ቺኩንጉንያ የተባለው የበሽታ ምልክት እስካሁን በ3 ሺህ 756 ሰዎች ላይ
ተስተውሏል።
ሆኖም ግን በሽታው ከወባ እና ከደንጌ ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ሁሉም ታማሚዎች ቺኩንጉንያ በተባለው በሽታ ስለመያዛቸው ሙሉ
በሙሉ እንዳልተረጋገጠም ነው ቢሮው ያስታወቀው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ከድር እንደተናገሩት፥ በ10 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ናሙና አራቱ ቺኩንጉንያ መሆናቸው
በመለየቱ በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ተረጋግጧል።
ከበሽታው ጋር በተያያዘ ግን እስካሁን የተመዘገበ ሞት እንደሌለም አስታውቀዋል።
ቺኩንጉንያ የተባለው በሽታ “ኤደስ” በተባለች ነብሳት አማካኝነት የሚተላለፍ መሆኑንም ነው ዶክተር ፉአድ ያስታወቁት።
በሽታው ከዚህ ቀደም በሶማሌ፣ በአፋር እና በደቡብ ክልሎች ተከስቶ እንደነበረ የገለፁት ዶክተር ፉአድ፥ ወደ ድሬደዋ ሊገባ የቻለውም
በበሽታው በተያዘ ሰው አሊያም በትንኟ አማካኝነት ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ከልዩ ምልክቶቹ መካከል ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት እና የጉልበት መገጣጠሚያዎች ከፍተኛ ህመም እንደሚያሳይ የገለጹ ሲሆን፥ ምልክቱ
የታየበት ሰው በአፋጣኝ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ህክምና ክትትል እንዲያደርግም አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የቺኩንጊኒያ ወረርሽኝን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ፉአድ አክለው
ገልፀዋል።
በዚህም 179 ሺህ በላይ በኬሚካል የተነከሩ የአልጋ አጎበሮች በከተማ እና በገጠር አካባቢዎች እንዲሰራጭ መደረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ተጠሪነቱ ለከተማዋ ከንቲባ የሆነ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየተሰራ ሲሆን፥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም እየተሰሩ
መሆኑን ነው ኃላፊው ያስታወቁት።
የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ቀንም ሆነ ማታ አጎበር ውስጥ መተኛት፣ የአካባቢውን ንጽህና እንዲጠብቅና ትንኝን ለማባረር የሚያገለግሉ የቆዳ
ቅባቶችን እንዲጠቀም አሳስበዋል።
ዶክተር ፉአድ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክትም በበሽታው የተያዘው ሰው በሽታውን በትንኝ ንክሻ
አማካኝነት ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላለፍ ቀንም ሆነ ማታ አጎበር ውስጥ መተኛት ፣ጤናማውም ሰው ቢሆን ሁሌም በሚተኛበት ጊዜ
አጎበር መጠቀም አለበት፤ ትንኝን ለማባረር የሚያገለግሉ የቆዳ ቅባቶችን መጠቀም፤ ወሀ ያቆሩ አካባቢዎችን የተጠናከረ አሰሳ
ማድረግና ህብረተሰቡን ስለበሽታው ግንዛቤ ማስጨበጥ፤እንዲሁም በአንድ አካባቢ የደንጊ ትኩሳት በሽታ መኖሩ ከተጠረጠረ በክልሉ
ለሚገኙ መንግስታዊና ህዝባዊ ድርጅቶች ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡