የ8ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተናዎች ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ ፈተናውን ያለምንም የፀጥታ ችግር ለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡ አዳዲስ የኩረጃ ዘዴዎችም ከወዲሁ ከሽፈዋል፡፡

0
903

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ እንዲሁም ክልላዊ ፈተናዎች ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ት/ቢሮ ከድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽንና ከድሬዳዋ አስተዳደር መምህራን ማህበር ጋር በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት ያለፉት አመታት ተሞክሮዎችን በመውሰድ በዘንድሮው አመት ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ የጋራ እቅድ በማዘጋጀት ከሚያዚያ 29 ጀምሮ በምክትል ከንቲባ የሚመራና 9 ተቋማትን በአባልነት የያዘ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም በርካታ የዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

13,372 ተማሪዎችን በ2011 ዓ.ም ለማስፈተን የሚረዱ 79 ጣቢያዎች በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት የድሬዳዋ አስተዳደር ት/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ ከሰው ኃይል፣ ከቁሳቁስና ከፋይናንስ እንዲሁም በፈተናው ወቅት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የማሟላት ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲሰጥ በፈተናው ጊዜ ተማሪዎች በራስ መተማመን እንዳይኖራቸው ሆን ተብሎ የሚነዙ ወሬዎችን አስቀድሞ ከማጥራት እንዲሁም ረቂቅ በሆነ መንገድ ዌብ ሳይቶችን በመጠቀም ለኩረጃ እቅድ የያዙ ተማሪዎች እንደነበሩ ገልፀው፤ ፖሊስ ቀድሞ በደረሰው መረጃ መሰረት ማጣሪያ ተደርጎ ሞባይልና አንዳንድ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ በፍተሻ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚደረግ በፈተና ላይ ምንም አይነት ስጋት እንዳይኖርና የጥበቃ እንዲሁም የፍተሻ ስራውም በከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚከናወን ፈተናው ይሰረቃል የሚል ስጋት ሳያድርባቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

 

ፖሊስ ኮሚሽነሩ የፖሊሶች ንቃተ ህሊና ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያየንበት በመሆኑ የዘንድሮውን አመት አገር አቀፍ ፈተና እንደ መልካም አጋጣሚ እናየዋለን ብለዋል፡፡

አቶ አበበ ታምራት የድሬዳዋ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ማህበራቸው 415 ከስነምግባር ጋር ተያይዞ ለገቡት ቃልኪዳን ታማኝ የሆኑና በስራቸው ውጤታማ የሆኑ ፈታኝ መምህራኖችን በመመልመል ለፈተና ዝግጁ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ ፈተናው ተሽጧል እንዲሁም መልሱ አስቀድሞ ወጥቷል እየተባለ ወላጆች ለልጆቻቸው አስቀድመው የፈተና ወረቀት እንዲገዙ ጭምር የሚነዙ ወሬዎች በሽያጩ ትርፍ የሚያገኙ ጥቂት ግለሰቦች ወሬ እንጂ እውነት አለመሆኑን ተገንዝበው በተለይም ወላጆችና መምህራን የተማሪዎች ስነ-ልቦና ግንባታ ላይ ትልቅ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here