የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሁሉም ማህበረሰብ ኃላነፊነት ነው ተባለ

0
434

በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን መስሪያ ቤት የአለም የአካባቢ ቀን በግልና በድሬዳዋ አስተዳደር “የአካባቢ ብክለትን እንከላከል” በሚል መሪ ቃል በአለም ለ46ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ26ኛ ጊዜ እንዲሁም በአስተዳደሩ ለ16ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅት ተከብሯል፡፡

 

በትላንትናው እለት በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ዝግጅት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብሩክ ግዛው እንደተናገሩት የአካባቢ ብክለት የተፈጥሮ ፀጋ እየተሟጠጠ የለጋሽ ሀገራትን ድጋፍና እርዳታ የምንጠብቅ እንድሆን አድርጎናል በማለት እንደ ሀገር እንደዚህ አይነት ችግርና ሰቆቃ ለመወጣት አካባቢያችንን ከመራቆትና ከብክነት በመጠበቅ የአረንጓዴ ልማትን በማፋጠን ከችግሩ መውጣት አለብን ብለዋል፡፡

የጽ/ቤቱ ኃላፊ አክለውም ድሬዳዋ ውብና ፅዱ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሚለውን ራዕይ ለማሳካት ሁሉም ማህበረሰብ አካባቢውን ከብክለትና ከቆሻሻ በማፅዳት በአረንጓዴ ልማት ተሳትፏቸውን  እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ በፓናል ውይይቱ እንደተናገሩት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድሬዳዋን ለማስዋብ  ለአራት አመት እቅድ ማቀዳቸውንና ወደ ስራ መግባታቸውን በመጠቆም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራም እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ከባለድርሻ አካላት ጋር ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተሻለ በቅንጅት በመስራት ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉት ታዋቂ አርቲስቶች ባስተላለፉት መልዕክትም ሀገራችንን ብሎም አካባቢያችን ከአካባቢ ብክለት ለመከላከል በግልም ሆነ በጋራ በመሆን ሁሉም ማህበረሰብ የድርሻውን ቢወጣ የአካባቢ ብክለቱን መከላከል ይቻላል ብልዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱም ላይ የፓናል ውይይት፣ የተለያዩ የጥበብ ስራዎችና የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር ዝግጅት እንዲሁም ከዚህ በፊት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኃላፊነት ላገለገሉ ኃላፊዎችና ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ ማህበራት ድርጅቶችና ተቋማት የእውቅና መስጠት ስነ-ስርዓት ተካሄዷል፡፡

በትዕግስት ቶሎሣ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here