ሁሉም የድሬዳዋ ወዳጆች ግብርን በአግባቡ በመክፈል እውነተኛ ተቆርቋሪነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ ቀረበ

0
691

“ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴንም እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 18-ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ለአንድ ወር በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚተገበር የታክስ ንቅናቄ በድሬዳዋ አስተዳደር ተጀመረ፡፡ የታክስ ንቅናቄው የመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይም በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ሚኒስቴር ዴታ የሆኑት አቶ መሐመድ አብዶ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐዲ ጊሪን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአስተዳደሩ ግብር ከፋይ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኘኝተዋል፡፡

 

የታክስ ንቅናቄው የመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ሚኒስቴር ዴታ አቶ መሐመድ አብዶ እንደተናገሩት በሀገራችን ባለፉት አመታት ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቶች ደካማ መሆን፣ የግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግንዛቤ ማነስ፣ የፖሊሲ ክፍተት፣ የታክስ ስወራ፣ ማጭበርበርና ኮንታፅባንድን የመሳሰሉ ስር የሰደዱ ችግሮች በመኖራቸው ሀገራችን ከግብር ልታገኝ የሚገባትን ገቢ በሚፈልገው መጠን መሰብሰብ እንዳይቻል ከማድረጉም በላይ ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥና ድህነት በልማት ድል ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ ቀላል የማይባል ተፅኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

አቶ መሐመድ አክለውም ግብርን በወቅቱ በታማኝነትና በተገቢው መጠን አሳውቆ ያለመክፈል የዜግነት የሞራል ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን በህግም እንደሚያስጠይቅ በመገንዘብ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ሁሉም የአስተዳደሩ አመራሮች፣ ግብር ከፋዮችና ነዋሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ የዜግነት ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በንቅናቄው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐዲ ጊሪ በበኩላቸው ግብርን መሰወርና ማጭበርበር ህዝብና ሀገር እንደመካድ የሚቆጠርና ሀገሩን ከሚወድ ዜጋ የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ሁላችንም የግብር ህጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከምንጊዜውም በላቀ ህዝባዊና የለውጥ መንፈስ በመታገል ያለብንን አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ በአግባቡ ለመወጣት ለአስተዳደራችንም ሆነ በሀገራችን ራዕይ ስኬት መረባረብ ይገባናል ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ የታክስ ንቅናቄ  ግንቦት 18/ 2011ዓ.ም ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በአስተዳደሩ ያለውን ገቢ የመሰብሰብ አቅምና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች እንዲሁም በታክስ ንቅናቄው ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ መሐመድ እንደተናገሩት ለመንግስት ከህዝብ ከተሰጡት ዋና ዋና አደራዎች መካከል አንዱ ህግና ሥርዓትን መሰረት በማድረግ ግብርን በመሰብሰብ እና በማስተዳደር በተገቢው አግባብ መልሶ ለህዝብ ጥቅማ መዋል መሆኑን ገልፀው የግብር ጉዳይ ምንም እንኳን የሁሉም አካላት ኃላፊነት ቢሆንም ግብር ከፋዩ እና ግብር ሰብሳቢ ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአስተዳደሩ ከ20,000 በላይ ግብር ከፋዮች እንዳሉ የገለፁት አቶ ካሊድ ምንም እንኳን በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በአስተዳደሩ ደረጃ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በ1998 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሰብሰብ የተቻለው አመታዊ ገቢ 53 ሚሊየን ብር እንደነበርና በ2011 ዓ.ም ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ በ10 ወራት አፈፃፀም ብቻ 887 ሚሊየን ብር በላይ(73.23%) መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይላሉ አቶ ካሊድ መሰብሰብ የተቻለው ገቢ ከተማችን ማመንጨት ከምችለው ገቢ ጋር ሲነጻፀር እንዲሁም በከተማዋ እየተነሱ ያሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመመለስ አንፃር እዚ ግባ የማይባልና ዘርፉ ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች በመፍታት የተሻለ ገቢን መሰብሰብ እንዲቻል እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

የግብር ስወራና ማጭበርበር፣ ህገ ወጥ ንግድ፣ የገቢ አሰባሰብ ስርዓታችን አለመዘመንና የተቋሙ ሰራተኞች አቅም ማነስ እንዲሁም የግብር ከፋዩ የግንዛቤ እጥረት የዘርፉ ዋንኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የገለፁት አቶ ካሊድ ችግሮቹን ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን ገልፀው ይህ የታክስ ንቅናቄ ፕሮግራምም የዚሁ ተግባር አንዱ አካል እንደሆነና እስከ ሰኔ 16 ድረስ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ የፓናል ውይይቶችና የመስክ ጉብኝቶች እንደሚካሄዱም ገልፀው ሁሉም የድሬዳዋ ወዳጆች ግብርን በአግባቡ በመክፈል እውነተኛ ተቆርቋሪነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here