የመብራት ፈረቃው ሰኔ 30 ድረስም ላይቆይ ይችላል ተባለ

0
847

በመላው ሀገሪቱ በተከሰተው የሃይል እጥረት ምክንያት የመብራት አገልግሎት በፈረቃ መሰጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ግድቦች ይሞላሉ ተብሎ ስለሚታመን እስከ ሰኔ 30 ድረስ ላይቆይም እንደሚችልና መብራት በመደበኛነት የ24 ሰአት አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል አቶ ሰለሞን ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የውሃ መጠኑ በቀን 30 ሴንቲ ሜትር እየቀነሰ ነው ያሉት ኃላፊው በዚህ ሁኔታ መብራት ለሁሉም ይድረስ ቢባል ከ1 ወር በኋላ በጭራሽ እንደ ሀገር መብራት አይኖርም ብለዋል፡፡ ስለሆነም የተወሰኑ ኃይሎችን መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የመብራት አገልግሎት በፈረቃ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
500 ሜጋ ዋት ኃይል መቆጠብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ያለንን ኃይል ለመቆጠብ በተቋም ደረጃ ባሉት 11 ሪጅኖች ምን ያህል መቆጠብ እንዳለባቸው ቀመር በወጣው መሰረት ድሬደዋም 15 ሜጋ ዋት ኃይል ለመቆጠብ ከተማዋን በ5 አቅጣጫዎች ከፍለው በ72 ሰዓታት ውስጥ ለ 8 ሰዓታት መብራት በማጥፋት እስከ ሰኔ 30 ድረስ ኃይልን የማመጣጠን ስራ እንደሚሰራ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡


የጅቡቲና የሱዳን የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት የኤሌትሪክ ሽያጭ የሱዳንን 100% የጅቡቲን ደግሞ 50% ለማቆም መገደዳቸውን በመጠቆም እንደ ተቋም ከዚህ የበለጠ ኪሳራ እንደሌለ በመግለፅ ከነዚህ ሀገራት የሚገኘው ከ180 ሚሊየን ዶላር በላይ ጥቅም ያጡበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎችና ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ በተለይም የጤና ተቋማት በልዩ ሁኔታ የመብራት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተቋሙ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በድንገት ባረጁ መስመሮች ጥገና ምክንያትና በተለያዩ ምክንያቶች ለሰዓታት መብራት የሚቋረጥበት ሁኔታ መኖሩን በማመን በ3ቱ አስቸኳይ የጥገና ማዕከላት ስልክ በመደወል ሪፖርት በማድረግ ካልሆነም ወደ ሪጅን በመደወል በአፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጥ በመግለፅ ከሽፍት ውጪ መብራት መጥፋት የለበትም ሊጠፋም አይችልም ብለዋል፡፡ መብራት የሚመጣበትና የሚሄድበት ሰአታት አንዳንዴ በትክክል ያለመሆን ነገሮች አሉ እሱ ላይም እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በስልክ ሪፖርት ለማድረግ ሲደወል ተደጋጋሚ ጊዜ አይነሣም ለሚለው ቅሬታ ስልክ የማይነሳ ከሆነ የደወሉበትን ሰዓትና ቀን እንዲሁም ምን ያህል ደጋግመው እንደደወሉ በመያዝ ወደ ተቋማችን መጥቶ ሪፖርት ማድረግ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በትዕግስት ቶሎሳ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here