በአስተዳደሩ ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ697 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል  ይህም የእቅዱ 87.6 በመቶ ያህሉ ነው፡፡

0
448

የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት 2ተኛ የስራ ዘመን 41ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ፡፡ በጉባኤው የአስፈፃሚ አካላት የ9 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የመስክ ምልከታ አስተያየት ቀርቦ በምክር ቤቱ አባላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት የአስተዳደሩ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ገቢ እስከ ሶስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ ከመንግስታዊ ታክስ 796,750,013 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የእቅዱን 87.55 በመቶ 697,522,868ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ጥሩ የሚባል አፈፃፀም ሲሆን የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አፈፃፀም ግን ከእቅዱ 32.93 በመቶ 98,784,525.38 ብር መሰብሰብ ብቻ መቻሉን ነው የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር መሃዲ ጊሬ የ9 ወራቱን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት 5ተኛ ዙር 41ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡበት ወቅት ያስታወቁት ፡፡ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አፈጻጸም አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም ክቡር ም/ከንቲባው ገልፀዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ውሎው የድሬደዋ አስተዳደር የውዝፍ ስራዎችና የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ለማቋቋም የወጣን አዋጅ እስከ 2012 ዓ/ም ለሁለት አመት እንዲራዘም ወስኗል፡፡ ምክር ቤቱ 3 አዳዲስ ሹመቶችን ያፀደቀ ሲሆን የተከበሩ አብዱልሰላም መሀመድ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ፣ የተከበሩ ስንታየሁ ማሞ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ፀሀፊ እንዲሁም የተከበሩ ኢብራሂም ዩሱፍ የግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ተሹመዋል፡፡

እንደዚሁም የ3 ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና 5 የተጓደሉ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሹመቶች ቀርበው በምክርቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን የድሬደዋ አስተዳደር ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ በመሆንም የተከበሩ አብዱሰላም መሃመድ ተሹመዋል፡፡

 

በበጀት ዓመቱ ሊሰሩ ከታቀዱት 16 የዘላቂ ልማት ግብ 23 የዩ ኤል ዲ ፒ  እና 150 የመደበኛ ካፒታል  በጠቅላላው 189 ፕሮጀክቶች የክትትልና ድጋፍ ስራ እየተከናወነ ቢገኝም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እየተተገበሩ ባለመሆናቸው ከፊሎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ለመጠናቀቅ ሰፊ ትኩረት የሚሹ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በተለይም ገና በቅድመ ዝግጅት ላይ የሚገኙትንና ሊተገበሩ የማይችሉትን 10 ፕሮጀክቶች እንዲታጠፉ መደረጉንም ነው አቶ መሃዲ በሪፖርቱ ያመላከቱት፡፡

በአስተዳደሩ ባለው መረጃ መሰረት 19,733 ስራ ፈላጊዎች በየቀበሌው የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7574 ወንድ እና 12,159 ሴቶች ናቸው፡፡ እስከ ሶስተኛ ሩብ ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ በተለያዩ ዘርፎች በተደረገው እንቅስቃሴ ለ9280 ቋሚ እና ለ7734  ጊዜያዊ ስራ እድል በአጠቃላይ ለ17,014 ስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሴቶች 2267 ቋሚ እና 2488 ጊዜያዊ በአጠቃላይ 4755 የስራ እድል ማለትም የ42% የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ም/ ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here