የድሬዳዋን የ20 ዓመታት የመጠጥ ውሃ ችግር ይፈታል የተባለው ፕሮጀክት ተመረቀ

0
584

የድሬዳዋን ህዝብ የዓመታት የንፁሁ መጠጥ ውሃ ጥያቄን ለ20 ዓመታት ይፈታል የተባለውና ከ9 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የንፁሁ መጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ተመርቋል፡፡ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መጀመሩን የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ተናገሩ፡፡

        የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ሥራዎች ባለሙያ አቶ መሊዮን ስብሃት ለኢዜአ እንደተናገሩት በአለም ባንክ ብድርና ድጋፍ እንዲሁም በአስተዳደሩ በጀት ላለፉት 6 ዓመታት የተገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

      ፕሮጀክቱ የመልካ ቀበሌን ሳይጨምር ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የከተማውን የውሃ ጥያቄ ማስተናገድ እንደሚችል ነው አቶ መሊዮን የገለፁት፡፡

       ፕሮጀክቱ 14 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች፤ እስከ 4 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ መያዝ የሚችሉ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች፣ 92 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ 12 ኪሎ ሜትር የውሃ ማደራሻ መንገዶች ተገንብተዋል ብለዋል፡፡

 

      ፕሮጀክቱ የዘመናት የነዋሪውን የንፁሁ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠቱ ባሻገር ለኢንቨስትመንትና ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ጥያቄዎችም ዕድገትም ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት፡፡

       በጨረታ መጓተት ከተቋራጭ አቅም ማነስ፣ ከካሳ ክፍያና ከቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች የተጓተተው ፕሮጀክት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ጀምሮ በከፊል አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበረ  አቶ መሊዮን ገልፀዋል፡፡

       ፕሮጀክቱ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ፣ የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የድሬዳዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል፡፡

        ለፕሮጀክቶቹ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና መ/ቤቶች እንዲሁም ግለሰቦችና አመራሮች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ መረጃውን ያደረሰን የኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here