የዓመታት የመጠጥ ውሃ ጥያቄያችን ምላሽ ማግኘቱ አስደስቶናልየድሬዳዋ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች

0
693

ከዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው አስተያየታቸው ለኢዜአ የገለፁት ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡

         አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩት የፌደራልና የድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለሁሉም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ፕሮጀክት የዓመታት የነዋሪውን የውሃ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው፤ ፕሮጀክቱ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ በጥንቃቄ እንደሚይዙት ነው ነዋሪዎቹ የገለፁት፡፡

        ሐጂ ሸምሸዲን ሙሣ እንደተናገሩት፤ በድሬዳዋ ሙቀት ለውሃ ችግር መጋለጥ ኑሮንና ማህበራዊ ህይወትን ያናጋ ነበር፣ አብዛኛው ነዋሪ በውሃ ዕጦት በአስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞውን ለዓመታት አሰምቷል ብለዋል፡፡

      ‹‹ዛሬ ያ ክፋ ጊዜ አልፎ ለዛሬው ቀን መብቃታችን ያስደስታል፤ እንደ አዛውንትነቴ ወጣቱን በማስተማር ውሃውን ለመንከባከብ ዝግጁ ነኝ ››ብለዋል፡፡

     ወ/ሮ ከበቡሽ አየለ ጀሪካን በመሸከም ውሃ ፍለጋ ሲንከራተቱ የነበረውን ጊዜ አስታውሰው በተለይ ለአንድ ጀሪካን ውሃ ለታክሲ ጨምሮ እስከ 20 ብር ያወጡበት ጊዜ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

        ‹‹የለገሃሬን ቀበሌ ነዋሪ ሄደህ ጠይቅ፣ ተማሪዎች ገላቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አጥተው ትምህርት የሚቀሩበት ጊዜ ነበር፤ ዛሬ ይህ ሁሉ በመቀየሩ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል›› ብለዋል፡፡

        ውሃውን እንደዓይናችን እንጠብቀዋለን፤ አንድም አደጋ እንዲደርስበት አንፈልግም ያሉት ደግሞ አቶ ዘሪሁን ጌታነህ ናቸው፡፡

         እሳቸው እንደተናገሩት በመንገድ፣ በቴሌኮምና በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች በአዲሱ ፕሮጀክት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስት ልዩ ክትትል ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

       ወ/ሮ አይሻ አብዱላሂ የዓመታት የንፁሁ መጠጥ ውሃ ጥያቄያችን ምላሽ ያገኘበት ቀን በመሆኑ ተደስተናል ብለዋል፡፡

         የቀበሌ ዘጠኝ ነዋሪዎች ውሃው ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ በገንዘብ፣ በጉልበታችንና በእውቀታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

     የሥራ ተቋራጩ አቶ አብዱረህማን ሙሜ የውሃ እጥረት በኮንስትራክሽንና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲፈጥር እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ቢዘገይም ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መጀመሩ በውሃ ሳቢያ በዘርፉ ላይ የሚደርስን ችግር መፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡፡፡

         የውሃ እጥረትና መጥፋት በብዛት ሲጎዳን የነበረው እኛ በአነስተኛ ምግብ ሥራ የተሰማራነው ሰዎች ነበር ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ሸዋዬ አበበ ናቸው፡፡

        ዛሬ በምረቃው ላይ የተገኘሁት የተሰማኝ ደስታ ለመግለፅ ነው፤ መንግስትን ለማመስገን ነው የመጣሁት›› ብለዋል፡፡

        በምረቃው ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የመልካ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አደን አህመድ የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት እነሱን ተጠቃሚ የማያደርግ በመሆኑ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

          ‹‹ውሃን በጀሪካን እየገዛን ነው በመጠቀም ላይ ያለነው፤ የቀሩት ደግሞ ወደ ሐረር ከሚሄደው ትልቁ ቱቦ የሚንጠባጠብን ውሃ በኮዳ ደቅነው እየተጠቀሙ ይገኛሉ፤ ይህን ችግር አስተዳደሩ በፍጥነት መፍታትና እኩል ተጠቃሚ ሊያደርገን ይገባል›› ብለዋል፡፡

          የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ መሐመድ ሙሣ የነዋሪዎቹ ስጋትና ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተናግረው በተለይ በሴክተሮች ቅንጅት ሳቢያ በመሠረተ ልማት ሃብት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመፍታት የተሻለ ቅንጅት ፈጥሮ መስራት ይገባል፤ ብለዋል፡፡

         ፕሮጀክቶቹን ወደ መልካ ጀብዱ ለማስፋትና የድሬዳዋን የውሃን ጨዋማነትን ለመከላከል ጥናቶች መጠናቀቃቸው ገልፀዋል፡፡

           ጥናቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚጠይቀውን ከፍተኛ ገንዘብ በአስተዳደሩ አቅም ብቻ የማይቻል በመሆኑ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ሌሎች ሚኒስቴር መ/ቤቶች እንዲሁም አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ሥራውን ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው አቶ መሃመድ የገለፁት፡፡

 

         የኢፌድሪ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በየደረጃው የሚገኘው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ፕሮጀክቱን በፍቅርና በፍትሃዊነት መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ  በተለይ በአፈርና ውሃ ጥበቃና ክብክቤ ሥራ ላይ ተቀናጀተው መሳተፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

         አስተዳደሩ በፍጥነት የመልካን የማስፋፊያ ፕሮጀክት መጀመር እንዳለበት አሳስበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

         ዛሬ ተመርቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የድሬዳዋ የውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡ መረጃውን ያደረሰን የኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here