ሉካንዳ ቤቶች የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አሰሙ መንግስት በበኩሉ ነፃ ገበያ ብንከተልም ህዝብ ሲመዘበር ዝም አንልም ብሏል፡፡

0
708

ሀገራችን ኢትዮጲያ የምትከተለው ነፃ ገበያ መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሆኑን ተከትሎ ከመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ውጪ ባሉት እቃዎች ላይ መንግስት የዋጋ ተመን ማስቀመጥ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህንን መብት በመጠቀም አንዳንድ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የህዝብን ኢኮኖሚ ሲያቃውሱ እየተስተዋለ ነው፡፡

      ከፋሲካ በአል ጀምሮ በተለያዩ የአስተዳደሩ አካባቢዎች በሚገኙ ሉካንዳ ቤቶች የ1 ኪሎ የከብት ስጋ ዋጋ እስከ 360 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ መረጃዎችን በመስማት ተዘዋውረን አይተናል፡፡ ተጠቃሚዎችም አማራጭ በማጣት እየገዙ እንደሆነና የግድ ስላልሆነም ሲያጡ ትተው በመሄድ ላይ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ ዋጋቸውን የጨመሩበትን ምክንያት ነጋዴዎቹ ሲገልፁ የከብት ዋጋ በመወደዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

     ይህንን ጥያቄ በመያዝ የአስተዳደሩ ፍትሀዊ ንግድ የስራ ሂደት ሄደናል፡፡ አቶ አህመድ አብደላ  የንግድ፣ ኢንስፔክሽን ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሰጡን ምላሽ ምንም እንኳን የምትከተለው ነፃ ገበያ መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢሆንም ህዝብ ሲመዘበር ዝም አንልም ብለዋል፡፡

       የበአል ሰሞን በአንዳንድ ማህበራዊ ድህረ ገፆች የከብት ዋጋ 98 ሺ ብር ስለገባ 1ኪሎ ስጋ ከ400 ብር በታች መሸጥ አያዋጣም ተብሎ የተለቀቀው መረጃ ቀድሞ ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰማ በማድረግ ነዋሪው ዋጋ ጭማሪውን ተቀብሎ እንዲገዛ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

      ፅ/ቤቱም ይህንን ተከትሎ ከ43 በላይ የሚሆኑ የሉካንዳ ቤት ባለቤቶችን በመሰብሰብ የከብት ዋጋው ቢጨምርም የተባለውን ያህል እንዳልሆነ በመተማመንና በማወያየት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ ከስምምነት ላይ ደርሰው መለያየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ይህንን ስምምነት በሚጥሱ ነጋዴዎች  ላይ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ካልታረሙ ንግድ ፍቃዳቸውን እስከመንጠቅና ስጋ ቤቱንም እስከማሸግ እርምጃ እንደሚወስድ  አስታውቀዋል፡፡

 

       የገበያ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ጥበበ ዘውገ በሰጡት ሞያዊ አስተያየት ዋጋ በጥራትና በቤቱ ሁኔታ ሊለዋወጥ ስለሚችል ህብረተሰቡ አቅሙ የሚችልበት ሄዶ እንዲገዛ ማድረግ እንጂ ነፃ ገበያ በምትከተል ሀገር ለምን ዋጋ ጨመርክ ብሎ ንግድ ቤቱን ማሸግ እንደማይቻል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

      የሀገር ውስጥ ገበያ ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ እሸቱ ኃይሌ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በራሱ ምርጫ በተመጣጣኝ ዋጋ ከሚሸጡት ላይ በመግዛት ዋጋ የሚያስወድዱትን ከገበያ ማስወጣት አንድ ዘዴ ቢሆንም መንግስትም እንደ መንግስት ስግብግብ ነጋዴዎችን እንደፈቀዳቸው ህብረተሰቡን ሲበዘብዙ ዝም ማለት እንደሌለበት በመጠቆም በመጀመሪያ በማስተማር አልመለስ የሚሉት ላይ ግን ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here