ፋሲካን ስናከብር ፍቅርን በተግባር በማሳየት እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች መከሩ ህዝበ ክርስቲያኑ ማህበራዊ እሴቶችን ለመታደግ ላደረገው ርብርብ ምስጋና ተችሮታል፡፡

0
669

በድሬዳዋ አስተዳደር የፋሲካ በዓል በልዩ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ዋና አዘጋጅነት በተዘጋጀው ልዩ የበዓል ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶችም ለነዋሪው ህዝብ የፋሲካ በአል ሲከበር ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን መስዋትነት በማሰብ ፍቅርን በተግባር በማሳየት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

     የሃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት የጋራ መልዕክት የፋሲካ በዓል ታላቅ ፍቅር የታየበት እንደመሆኑ መጠን በዓሉን ስናከብር ከወገኖቻችን ጋር በሰላም ለመኖር፣ ለመዋደድ፣ ለመከባበርና ለአንድነት ዝግጁ በመሆን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ የታመሙና በእስር ላይ ያሉ ወገኖችን በመጠየቅ፣ የታረዙን በማልበስ፣ የተራቡን በማብላት እንዲሁም በፆም ወቅት ሲደረጉ የነበሩ በጎ ምግባሮችን ሁሉ በህይወት ዘመናችን  ለሰው ልጆች ለማድረግ ቃል የምንገባበት በአልም እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል፡፡

     ድሬዳዋ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የመቻቻል ከተማ በመባል የምትታወቅ የነበረበት ጊዜ መልኩን እየቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት እንደዚህ ያለውን ሃይማኖታዊ በአል በጋራ ለማክበር በድሬዳዋ ራስ ሆቴል በተዘጋጀው ልዩ የበዓል ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለብርሃነ ትንሳኤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

     ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት የትንሳኤ በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገር በቀጣይ ድንቅ የጋራ እሴት የሆነውን የኃይማኖት ብዝሃነትን በማጎልበት በአንድነት ለመኖር ያለን ተስፋ የሚንፀባረቅበት ነው ብለዋል፡፡

     አቶ ከድር ጁሃር አክለውም በሃገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት በአስተዳደራችንም የተስተዋለ ቢሆንም ህዝበ ክርስቲያኑ ግን ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር የመቻቻል፣ የወንድማማችነት፣ የአብሮነትና የፍቅር ማህበራዊ እሴቶችን ለመታደግ ላደረገው ርብርብ ያላቸውን ምስጋናና አክብሮት በአስተዳደሩ ስም አቅርበዋል፡፡

     በአሉ የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስትና የድርጅት አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች ጥሪ የተደረገላቸው የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here