በአስተዳደሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዳለ ነዋሪዎች ጠቆሙ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መፍትሄ ተበጅቶለታል ብሏል፡፡

0
666

በድሬደዋ አስተዳደር የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መምጣቱን በተለያዩ የከተማዋ ቀበሌዎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልፀውልናል፡፡ በከተማዋ የሚኖሩ ነዋሪዎች በተለይም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እንደገለፁት የአገልግሎት ተደራሽነቱም ቢሆን ከቀድሞው የተሻለ ይሁን እንጂ አሁን ድረስ ለሳምንት ያህል የሚጠፋበት ጊዜ እንዳለ በማሪያም ሳይት ኮንዶሚኒየም ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ ትዕግስት ተናግራለች፡፡

     የድሬደዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን መስሪያ ቤት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ 16 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማስቆፈር ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገልጿል፡፡

      ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር በአስተዳደሩ የተጀመረው ጥልቅ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ የሙከራ ስርጭት ጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ በሶስት አመት ውስት ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረ ቢሆንም ከጨረታ ጋር ተያይዞ፣ በኮንትራክተር አቅም ማነስ፣ ፕሮጀክቱ ግዙፍ በመሆኑ የውስጥ የማስፈፀም አቅም ውስንነት እንዲሁም መስመር የሚያልፍባቸው እና ጉድጓድ የሚቆፈርባቸው ቦታዎች የይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያየዞ በተከሰተ ችግር ፕሮጀክቱ ከታቀደለት ጊዜ በላይ ጊዜ ወስዶ በአምስተኛ አመቱ መጠናቀቁን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የውሃ አቅርቦትና ስርጭት አብይ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ካሚል ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡

 

እንደ ስራ ሂደት መሪው ገለፃ በአሁኑ ወቅት ቀፊራ  07፣ 02፣ 09 ቀበሌ አዲስ ከተማ እንዲሁም ለገሀሬ አካባቢ በከፊል ውሃ እያገኙ እንዳሉ ገልፀዋል፡፡ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ችግሮች እንደገጠማቸው የገፁት አቶ ካሚል ይህንንም ለመቅረፍ በተለይ በገንደ ቦዬና 04 ቀበሌ ግሪን ካምፕ እንዲሁም ከዚራ ላይ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

    ኃላፊው አክለውም ባለፉት 10 ቀናት በቀበሌ 05 ኮኔል አካባቢ ከመብራት ጋር ተያይዞ ችግር እንደገጠማቸው ጠቅሰው ይህንንም ለመፍታት ከተቋሙ ጋር እየሰሩ እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

     ከውሃ ጥራት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ችግር አቶ ካሚል ሲመልሱ ጉድጓዶች እርስ በርስ ሲገናኙ እና ጥገና ሲካሄድ በነዚህ ሁለት ምክንያቶች የውሃ መደፍረስ እንደሚከሰት ገልፀው፤ ይህም ሲሆን ጥራቱን ለማስጠበቅ የደፈረሰውን ውሃ ወደ ውጪ በማፍሰስና የተለያዩ የማከሚያ ዘዴዎች በመጠቀም ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ በአይ ኤስ ኦ የጥራት ደረጃ ያለውና የጨዉም መጠን ቢሆን ወፈር ብሎ ለጉሮሮ ይከብድ እንደሆነ እንጂ በተገቢ ሁኔታ ታክሞ ደንበኞች ጋር ስለሚደርስ ጤና ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደሌለው በመግለፅ የጥራት ደረጃው ላይ ነዋሪው ጥርጣሬ እንዳይገባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here