ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ስልጣናቸውን ለምክትል ከንቲባ መሀዲ ጊሬ አስረከቡ

0
736

ላለፉት ሶስት አመት ተኩል ድሬዳዋን በከንቲባነት ሲያስተዳድሩ የቆዩት ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በድርጅታቸው ኢሶህዴፓ ለሌላ ኃላፊነት በመታጨታቸው መንበረ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡

በከንቲባ ማዕረግ ምክትል ከንቲባ ሆነው ድሬዳዋን እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት አቶ መሀዲ ጊሬ በ1974 በሽንሌ ሲቲ ዞን የተወለዱ ሲሆን እድገታቸው ድሬዳዋ ላይ እንደሆነ ተነግሮላቸዋል፡፡ ባለ ትዳርና የ 4 ልጆች አባት የሆኑት አቶ መሃዲ በፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ማስተርስ ያላቸውና በዩኒቨርሲቲ መምህርነት፣ በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ቢሮ ኃላፊነት፣ በኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ፣ በኢፌድሪ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተመጣጣኝ ልማት አማካሪ እንዲሁም የሽንሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ በመሆን ድርጅትና ህዝብን ያገለገሉ አመራር ናቸው፡፡ ምክትል ከንቲባው በቀጣይ ድሬዳዋን ለማስተዳደር በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሀላ ፈፅመው ከቀድሞ ከንቲባ ጋር ርክክብ አድርገዋል፡፡

መጋቢት 3/2012 በተካሄደው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ አባላት 7 ሹመቶችን አፅድቀዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው የተሾሙት አቶ አብደላ አህመድ ሲሆኑ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ደግሞ አቶ ከድር ጁሀር በመሆን ተሹመዋል፡፡

ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ሙሳ ጣሃን የፍትህ፣ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም አቶ አብዱሰላም አህመድን የግብርና እና ውሃ ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ መርጧቸዋል፡፡

ነባሩ ከንቲባ በመሰናበቻ ንግግራቸው እንደ ድሬዳዋ ተወላጅነታቸው በነበራቸው የስልጣን ጊዜ ሁሉ ለህዝቡ ይበጃል ያሉትን ሲሰሩ እንደነበር በመግለፅ፣ በአመራርነት ባገለገሉበት ወቅት ላሳዘኑትና ቅር ላሰኙት አካል ሁሉ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በቀጣይም የስራ ዘመናቸውም ቢሆን ድሬዳዋ ላይ ያሉ አመራሮችን ባላቸው አቅም ሁሉ እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል፡፡ ለአዲሱ ከንቲባም መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡

አዲሱ ከንቲባ አቶ መሀዲ ጊሬም ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው ያላቸውን የሥራ ልምድና የአዲሱን ካቢኔያቸውን እምቅ ኃይል በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚተጉ በመግለፅ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ በመስጠት ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here