የከተሞች ፎረም ህዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ተናገሩ

0
845

የከተሞች ፎረም በከተሞች ህዝቦች ንቅናቄን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 8ኛው የከተሞች ፎረም በጅግጅጋ ከተማ የመክፈቻ ስነ-ስርአቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

ፎረሙን በንግግር የከፈቱት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እለቱ በከተሞች ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር የሚያስችል መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው በከተሞች ሁሉን አቀፍ ልማት ማስመዝገብ የሚቻለው ጠንካራ አጋርነት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ሲኖር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

እለቱም በከተሞች የልማት ስራ ላይ በነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት መካከል ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ይከበራል ብለዋል፡፡ በከተሞች መካከል ጤናማ ውድድር ለመፍጠርና ከተሞች እርስ በእርስ ልምድ እንዲለዋወጡ እንደሚያስችል ጠቅሰው በነዋሪው ዘንድም የባለቤትነት መንፈስ ያሳድራልም ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የነዋሪውን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ እረገድ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ጋር በማያያዝ ፕሬዝዳንቷ ለከተሞች ግብአት የሚሆኑ ፈጠራዎች የሚታዩበት እንደሆነም ጠቅሰዋል ፡፡

ፕሬዝዳንቷ በከተሞች የሚታየውን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለማሻሻል የዘርፉን ተልዕኮ ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራር ተቀርፎ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዘንድሮ የከተሞች ቀን በጅግጅጋ ከተማ መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልፅግና በሚል መሬ ቃል ከየካቲት 9 እስከ 14 /2011 ዓ.ም ድረስ ይከበራል፡፡

ፎረሙ በፓናል ውይይት፣ በባህል ልውውጥ፣ በከተሞች አውደርዕይ እና በተለያዩ ትርዒቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዘንድሮ ፎረም ላይ ከሀገር ውስጥ 167 ከተሞች ተሳታፊ ሲሆኑ 6 የጎረቤት ሀገራት ከተሞች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ስድስት ድርጅቶች እና ከ10 በላይ ተባባሪ የመንግስትና የግል የልማት ድርጅቶችም የዘንድሮ ፎረም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

በትእግስት ቶሎሳ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here