አረጋዊያን ድርብ ክብር ይገባቸዋል

0
762

አረጋውያን የዕድሜ ባለጸጋና ናቸው፡፡ በዚህ ዕድሜያቸው ውስጥ የታመቁ ዕውቀቶች፣ ልምዶች እና ጥበቦች ይገኛሉ፡፡ ዕድሜ ከቀለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እና በኑሮ በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተምሯቸዋል፡፡ አረጋዊያን በወረቀት ላይ ሳይሆን በልቦናቸው የተጻፉ የበርካታ ጠቃሚ ታሪኮች ባለቤትም  ጭምር ናቸው፡፡ ባጠቃላይ አረጋዊያን ሀገር ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለዚህ ሀገር ማለት ሰው ነው ብለን ከተግባባን አረጋዊያን በእርግጥም ሀገር ናቸው፡፡

 እንግዲህ ጠጋ ብሎ በታላቅ በአክብሮት ላዳመጣቸው ተዝቆ የማያልቅ የዕውቀት፤ የጥበብ እና የልምድ ምንጭ መሆናቸውን መረዳት አያስቸግርም፡፡ አንድ በጣም ታዋቂ የሆነ የዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ በአንድ ወቅት የምድራችን ትልቁ ሀብት የት እንደሚገኝ ታውቃላችሁ ብሎ ተማሪዎቹን ጠይቆ ነበር፡፡ እናም ተማሪዎቹ ብዙ ሞክረው መመለስ ቢያቅታቸው በመቃብር ነው ብሎ መልሶላቸው ነበር፡፡ ምክኒያቱም ብዙ አረጋዊያን በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድና የቀሰሙትን ትምህርት ይዘው ስለሚሞቱ ነው፡፡

ይህ አስገራሚና የሚቆጭ እውነት ዛሬም በግልጽ የሚስተዋል ጉዳይ ነው፡፡ አረጋዊያን ያካበቱትን ትልቅ የአእምሮ ሀብት ጠጋ ብለን እንደዋና ሀብት ሳንወርሰው ቢሞቱ ምን ያህል ይቆጫል? እሱም እኮ መደመጥ ይፈልጋሉ፡፡ አደራ ሊሰጡን የሚፈልጉት በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች አሏቸው፡፡

 ከዚህም በተጨማሪ አረጋዊያን ራሳቸው ክብራችን ናቸው፡፡ እነሱ ያልተገኙበት የትኛውም ባህላዊ፣መንግስታዊ እና ህዝባዊ ሁነት ክብር ይጎድለዋል፡፡ በአንጻሩ ግን እነሱ የታደሙበት እና የመረቁት ሁነት ምን ያህል  ስኬታማ፣ ድባቡም ክብር ያለው እንደሆነ በተግባር ማየት እና ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አረጋዊያን ያልተገኙበት በዐልና ሸንጎ ሞገስ እንደሚጎለው ሁሉ እነሱ ያልተገኙበትና ያልመረቁት የትኛውም ሀገራዊ አጀንዳ ለውጤት ሊበቃ አይችልም፡፡ ምክርና መላ ከአረጋዊያን አይጠፋም፡፡ ተናግረው የሚያሳምኑበት ርቱዕ አንደበት አላቸው፡፡

አረጋዊያን የዚህች ሀገር ትልቅ ባለውለታ መሆናቸው ሌላው  እንድንንከባከባቸውና እንድናከብራቸው የሚያደርገን በቂና አሳማኝ ምክኒያት ነው፡፡ ማን ያውራ የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ በአፍሪካ ብሎም በዓለማችን አደባባዮች ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ለማቆየት ያልወጡት ዳገት፣ ያለወረዱት ቁልቁለት እንደሌለ ታሪካቸው በወረቃማ ብዕር ተጽፎላቸዋል፡፡ እኛ በነጻነትና በክብር እንድንኖር ከህይወት፣ ከደምና ከአጥንት ትልቅና ውድ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

ስለሆነም አረጋዊያን ከማንም በላይ እጥፍ ድርብ ክብር ሊሰጣቸውና  እንክብካቤ ሊደረግላቸው የሚገባቸው ናቸው፡፡ አረጋዊያን ወገን እያላቸው እንደሌላቸው ተርበው፣ታርዘው እና ለጎናቸው ማረፊያ አጥተው ሲንገላቱ ማየት ምን ህል ያማል፡፡ አረጋዊያን በራሳቸው ወገን በአደባባይ ሲዋረዱ ማየት ልክ ሀገር እንደተዋረደች ያህል ሊያንገበግበን ይገባል፡፡

የመንግስትኮሙዩኒኬሽንጉዳዮችቢሮ

                                                                                      ድሬዳዋ

                                                   22/04/2011ዓ/ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here