ትክክለኛ ለውጥ ከራስ ይጀምራል

0
844

ሀገራችን አጓጊ፣ተስፋ ሰጪ እና አስደማሚ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ውጤቶች የተመዘገቡበት የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡ መንግሥት በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ አክቲቪስቶችን ከእስር ፈትቷል፡፡ በአገር ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ጋርም በለውጡ ዙሪያ ሠፊ ውይይትን አድርጓል፡፡ በውጭ አገራት ተሰደው የነበሩ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

 ሌላው ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና ለአገሪቱም ሆነ ለአካባቢው ሠላምና ጸጥታ መስፈን ከፍተኛ አሰተዋጽኦ የሚያደርገው ከኤርትራ ጋር ቀድሞ የነበረውን መጥፎ ታሪክ ለመቀየር እና በምትኩ በአፍሪካ ቀንድ በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚችል ለሠላም ስለ ሠላም መንግሥት የወሰደው እርምጃ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከቃል ያለፈ እና በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትልቅ መተማማንን ሊፈጥር የሚችል እርምጃ ተዋስዷል፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስፈን ትልቅ  ሚና የተጫወቱ ሕጎችን  የማሻሻል ሥራም የተጀመረ ሲሆን፣ የፍትህና የፀጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሠፋ ያለ ተቋማዊ የመዋቅር ማሻሻያዎችም ተደርገዋል፡፡

እነዚህ በተከታታይ የተወሰዱ በጎ እና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች  አዲስ የለውጥና የሽግግር መንፈስ በአገሪቱ እንዲሰፍን አድርገዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት የሚገርመው እና የሚያሳዝነው ለውጡን የሚያደናቅፉ፤ በሕዝቦች መካከል መቃቃርን፣ ጥላቻን፣ አለመተማመንንና መነጣጠልን ያስከተሉ በርካታ ሥርዓት አልበኛ እንቅስቃሴዎች፣ ግጭቶችና ብጥብጦች መከሰታቸው ነው፡፡

ይህ ለውጥ እንዲመጣ ወጣቱ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ወጣቱ ለውጥ ፈላጊ መሆኑን ከመናገር ባለፈ በተግባር እያረጋገጠ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ለውጥ ሊያደናቅፉ የሚችሉና በተለይ በአሁን ወቅት የላቀ ትኩረት የተሰጠውን የአገራዊ አንድነት ግንባታ ሂደት በተፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ እያደረጉ የሚገኙ ክስተቶች ከየት መጡ? ከጀርባ ሆኖ እነዚህን ክስተቶች የሚያቀነባብረውስ ማነ ነው? ብሎ ወጣቱ ሊጠይቅ ይገባል፡፡

ስለሆነም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ግለሰብ ስለ ለውጡ ማውራት እና ከለውጡ ጋር ራስን ለመለወጥ ቁርጠኛ መሆን ሁለት የሚለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ለውጥ ከራስ ይጀምራል እና ለውጡ ያመጣውን ጥሩ ዕድል በመጠቀም ራሳችንን ለመለወጥ ቁርጠኛ እንሁን፡፡

የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         13/05/2011ዓም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here