በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ስምምነት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ከእንስሳት ሃብት ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችልም ተገልፃል፡፡

0
881

በኢትዮጲያና ጅቡቲ ድንበር አካባቢዎች የእንስሳት ጤናን በመጠበቅና አስተማማኝ የንግድ ስርዓትን በመዘርጋት የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ሁለቱ ሀገሮች በድሬዳዋ አስተዳደር ተፈራረሙ፡፡

ድንበር ተሻጋሪውን የእንስሳት ጤና እክብካቤና የጋራ ተጠቃሚነት ሰነድ የፈረሙት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ግብርና ሚኒስቴር አቶ ዑመር ሁሴንና የጅቡቲ እርሻ ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ታባረክ መሐመድ ናቸው ፣ በዚሁ ጊዜም ሀገራችን ጤናማ የአንስሳት ሃብትን ለአለም ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆንና በእንስሳት ሃብት አጠቃቀም ላይ ጋሬጣ እየሆነ የሚገኘው በድርቅ ወቅት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው በፍጥነት በመዛመት በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት የሚያሳጣው የእንስሳት በሽታን ችግር በጋራ ለመከላከልና አስተማማኝ የንግድ ስርዓቱን በመዘርጋት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ስምምነቱ ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው የኢ.ፌ.ድ.ሪ ግብርና ሚኒስቴር አቶ ኡመር ሁሴን ገልፀዋል፡፡

ሚኒስተሩ አክለውም ስምምነቱ ሁለቱ ሀገሮች በሚጋሯቸው አካባቢዎች ያለውን ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ጤና በመጠበቅና ተወዳዳሪ የእንስሳት ምርቶችን ወደ ተቀባይ ሀገሮች በመላክ የሀገርና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግና በስምምነቱ መሰረትም የሚተገበሩ ስራዎች ሀገራችን ወደ ውጭ የምትልካቸውን ዝቅተኛ ምርት እንዲጨምር በማገዝ በዘርፉ ያሉትን የአቅም ውስንነት የሚፈታ ይሆናል ብለዋል ፡፡

በጅቡቲ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የጅቡቲ እርሻ ሚኒስትር ቴክኒካል አማካሪ ዶክተር ታባረክ መሐመድ በአሁን ወቅት ጅቡቲ በርካታ የቀንድ ከብት ሀብት እንዳላትና ስምምነቱም በተለይም የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ጠቅሰው ይሄም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃትና ለድህነት ቅነሳው አጋዥ እንደሆነ ተናግረው በቀንድ ከብት ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ተላላፊ የእንስሳት በሽታዎች በመስፋታቸው በቀጣይ በጋራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በሰምምነቱ መሰረት ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጀምሮ ለ5 ዓመታት የእንስሳቱን ጤና ለመጠበቅ፣ እቅዱን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ዝርዝርና ስትራቴጂ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ ለሥራው ማስፈጸሚያ የሁለቱ ሀገሮች ከሚመድቡት በጀት በተጨማሪ ኢጋድ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮች በማፈላለግ ለስራው መሳካት ድጋፍ እንደሚያደርግ በስምምነቱ ላይ ተገልፃል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here