ለችግሮቻችን ባለቤት እና አድራሻ ልናበጅላቸው ይገባል

0
777

የመልካም አስተዳደር ችግሮችም አንበላቸው ሌሎች ችግሮች  የአስተዳደራችን  አሊያም የሀገራችን ችግር የሚሆኑት ትንንሽ  የምንላቸው ችግሮች እየተደመሩ  ሲሄዱ ነው፡፡ ችግሮች ደግሞ እየተደመሩ የሚሄዱት  ትክክለኛ አድራሻቸው ባለመታወቁ ነው  አለበለዚያም  ለችግሮቹ ያለን ግምት የተሳሳተ ከመሆኑ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋራ ተያይዞ ችግሮቻችንን  በባለቤትነት ስሜት ለመፍታት ያለመንቀሳቀስ በራሱ እንደ አንድ ችግር አድራሻና ባለቤት ሊፈለግለት ይገባል፡፡

የትኛውም ችግር ያራሱ  አድራሻ እና ባለቤት የሌለው ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ችግር የራሱ በቂ ምክኒያት እና መነሻ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ህዝብም መንግስትም በየመድረኩ እና በየስብሰባው በችግርነት የሚያነሳቸው ጉዳዮች ምንጫቸው ታውቆ ከምንጫቸው ሊደርቁ ይገባል፡፡

ለሁሉም ችግሮቻችን ትክክለኛ አድራሻ እና ባለቤት መስጠቱ ችግሮቻችንን ለመፍታት  የምንጓዘውን ርቀት ግማሹን የማጠናቀቅ ያህል ነው፡፡ ችግሮቻችንን በትክክል እና በመረጃ በተደገፈ አካሄድ አድራሻቸውን ካገኘን ቀጣዩ እና ዋናው ሥራ የኃላፊነትን እና  የተጠያቂነትን አሠራር መዘርጋት ይሆናል፡፡

የኃላፊነት እና የተጠያቂነትን አሠራር ስንዘረጋ የህዘብን ጥቅም ለድርድር ከሚያቀርብ ተቀጽላ አሠራር በጸዳ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ በጋራ ለመልማት እና ነገ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ህዝብ እና መንግስት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለለውጥ በሚረባረቡበት በዚህ ወቅት አላስፈላጊ ተልካሻ  ምክኒያቶችን በመደርደር ችግሮቻችን ሳይፈቱ ሌላ ችግር እንዲወልዱ ጊዜ መስጠት አይገባም ፡፡

አምና ያወራናቸውን ችግሮች ዘንድሮም ደግምን የምናወራቸው ከሆነ የዕድገት እና የለውጡ ውጤት በምን ሊለካ ነው? እርግጥ ነው አንዳንድ ችግሮች ውስብስብ እና አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ሁሉንም ችግሮች አድራሻቸውን እና ምንጫቸውን በመለየት እንደባህሪያቸው የጋራ ርብርብ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡

                                         

                                            የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       03/05/2011ዓ.ም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here