ድሬ ኢንፎ በሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሁርሶ ላለፉት ሶስት ወራት ለ 6ተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰባት ሰላም አስከባሪዎችን አስመርቋል፡፡

0
1400

የእለቱ ተመራቂዎችም ሀገራቸውን ወክለው በሚሰማሩበት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ሁሉ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት ያለውን ውጤታማ አፈፃፀም የማስቀጠል ሀላፊነት እንዳለባቸው በምርቃቱ ላይ ተገልፃል፡፡

አለም አቀፍ የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአለማችን ላይ ከተጀመረ ወዲህ ሀገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ 1951 ጀምሮ በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ ከግንባር ቀደሞቹ የአለም ሀገራት አንዷ በመሆን ለአለም ሰላም መስፈን የበኩሏን ስትበረክት ቆይታለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ እየተሰማራ የሚገኘው የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ግዳጆች ባሉበት በሱዳን ዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳን፣ በአብዬና በሶማሊያ በርካታ ኮንቲንጀንት ሻለቆችን በማሰማራት ውጤታማ የሆነ የሰላም ማስከበር ግዳጅ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡

በሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሁርሶ ላለፉት ሶስት ወራት ለ 6ተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰባት ሰላም አስከባሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ተመራቂ ሰራዊቶችም ደቡብ ሱዳን፣ ዳርፉር እንዲሁም በአብዬ አለም አቀፍ ሰላም ለማስከበር የሚዘምቱ ይሆናል፡፡

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ በመገኘት ለተመራቂዎች ንግግር ያደረጉት በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የህብረት መረጃ ዋና መምሪያ ሀላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ሌተናል ጀነራል ሀሰን ኢብራሂም የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ለአህጉራዊና አለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራዊቶችን በንቃት በማሰማራትና ውጤታማ የሆነ አፈፃፀምን በማስመዝገብ በተለያዩ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ እውቅናና ከበሬታን እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ክቡር ሌተናል ጀነራል ሀሰን ኢብራሂም አክለውም የእለቱ ተመራቂዎች ሀገራቸውን ወክለው በሚሰማሩበት ሀገራት ሁሉ ውጤታማ የሆነ አፈጻፀም በማስመዝገብ በድል እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡

ተመራቂ የሰራዊት አባላት በሚሰማሩበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ የሚገጥሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች በአሸናፊነት ይወጡ ዘንድ ላለፉት ሶስት ወራት ከፍተኛ ጥራትና ብቃት ያለው የግዳጅ አፈፃፀምን እውን በማድረግና በተግባርም ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተልዕኮ ተኮር የሆኑ ስልጠናዎችን መውሰዳቸውን በሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ተወካይ ኮረኔል ሚልኬሳ ረጋሳ ገልፀው ሰራዊቱ የተጣለባቸውን ግዳጅ በመወጣት ሀገራችን በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር የግዳጅ አፈፃፀም ላይ ያላትን እውቅና ማስጠበቅ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

በተሰማሩበት የግዳጅ መስክ ሁሉ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በእለቱ ተመራቂ የሆኑ የሰራዊት አባላት ተናግረዋል፡፡

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የተገኙ ሲሆን ለተመራቂ ሰላም አስከባሪ ሬጅመንቶች ከእለቱ የክብር እንግዳ የእውቅና ሰርተፍኬት ተብርክቶላቸዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here