ሁላችንም ለሠላም አምባሳደር ልንሆን ይገባል

0
758

የሠላምን ዋጋ ከእኛ ከኢትየጵያዊያን በላይ በቅጡ ሊረዳ የሚችል ሊኖር አይችልም፡፡ ለረጅም ዓመታት በውጪ እና በውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ስንናጥ ከኪሳራ፣ ኋላ ቀርነት እና ድህንት በቀር ያተረፍነው ነገር የለም፡፡ ከዚህም የተነሳ ሠላምን ማጣት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን የምናውቀው እንደሌሎቹ በሚዲያ ሳይሆን ካጠገባችን በተለዩን ዘመዶቻችን እና ወገኖቻችን ነው፡፡ ለዚህም ነው ስለሠላም ዋጋ ከእኛ በላይ አዋቂ ሊኖር አይችልም ብለን በድፍረት የምንናገረው፡፡

ሀገራችንን ከገባችብት የኋላ-ቀርነት እና ድህንት ለማውጣት እንኳን ቀልባችንን ሰብሰብ አድርገን በጋራ ውጤት ያለው ሥራ ለመሥራት መረጋጋት አልቻልንም፡፡ አሁንም በአስገራሚ እና አጓጊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ እያለን እንኳን በእርስ በእርስ ግጭት ያሳለፍናቸው እነዚያ ያለፉ ወርቃማ ጊዜያት ሊቆጩን ሲገባ በትንሽ ትልቁ መጋጨታችን አላቋረጠም፡፡

ይህ ሁኔታ ለሠላም ዋጋ የከፈሉ አባቶቻችንን እና ወዳጆቻችንን በእጅጉ የሚያሳዝን ሁቤታ ነው፡፡ ታዲያ እንደ ሀገር መቼ ይሆን ይበቃናል ብለን በማምረር ሠላማችንን ጠብቀን እያጠናከርን የምንሄደው? ይህ መሠረታዊ እና የአጀንዳዎቻችን ሁሉ ዋና የሆነው የሠላም ጥያቄ የሁላችንም ተቀዳሚ ጥያቄ ሊሆን ይገባል፡፡

የሁላችንም የድሬዎች መኖሪያ የሆነችው ድሬ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ጫፍ እስከ ጫፍ የምትታወቀው በፍቅር በመቻቻል እና በአብሮነት ነበር፡፡ ድሬ እንኳን ሰው ወፍ ታለምዳለች እንዳልተባለልን ዛሬ ዛሬ ግን ድሮ ያልተሰሙ ግጭቶችን እና ሞቶችን የምታስተናግድ መሆኗ የእኛን ብቻ ሳይሆን ድሬን ለሚያወቋት ሁሉ ልብን የሚሰብር ክስተት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ቀደመው ዝናችን እና ማንነታችን ልንመለስ ይገባል፡፡ ያጣነው የድሮው መልካም ስማችን በሁላችንም ጥረት እና ርብረብ ሊመለስ ይገባል፡፡

ስለሆነም ሁላችንም ለሠላም ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ ስለሠላም ከቤት፣ከሰፈር ወይም ከአካባቢ፣ ከቀበሌ ብሎም እስከ ሀገር ድረስ መሥራት ያለብንን ለመሥራት ያለማንም ቀስቃሽ ልንንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ስለሠላም እየዘመርን ስለሠላም እያስተማርን ሳያወቁ ሠላም የሚያደፈርሱትን ከክፉ ድርጊታቸው ልናስቆማቸው ይገባል፡፡

እያወቁ የጥፋትን መንገድ የሚመርጡትን ደግሞ ተከታትለን ከህግ እና ፍትህ  ተቋማት ጋር በመቀራረብ ህግ ፊት ልናቀርባቸው ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ ሠላማችንን ልናረጋገጥ የሚገባን እና መልሶ እንዳይደፈርስ የመጠበቁ ኃላፊነት የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                        12/04/2011ዓም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here