ልዩነቶቻችን ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን እንጂ የግጭት መንስኤዎች ሊሆኑ አይገባም!!!

0
680

ልዩነቶች ከነባራዊ ሁኔታዎቻችን አሊያም ከዝንባሌዎቻቻንና ከፍላጎቶቻችን የሚመነጩ የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው ፡፡ ከዚህ አንጻር ምንም ዓይነት ልዩነቶች ከተፈጥሯዊ ማንነታችንና ከዕምነታችን ስለሚመነጩ በአስተሳሰብና በተግባራችን ሊገለጡ ይችላሉ ፡፡ እነዚህ ልዩነቶቻችን አንዳንዶቹ ገና ከጠዋቱ ስንወለድ ጀምሮ አብረውን የነበሩ በመሆናቸው ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከጊዜ በኋላ በመኖር ሂደት አምነንባቸው የተቀበልናቸው ስለሆኑ ከማንነታችን ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው ፡፡

        ስለሆነም እነዚህን ልዩነቶች ሌሎች ሲያከብሩልንና ሲያደንቁልን አንጂ በተቃራኒው ሲያንቋሽሹብንና ሲያጣጥሉብን ስሜታችን ስለሚጎዳ በመስተጋብራችን ላይ ይህ ነው ሊባል የማይችል አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ ፡፡ ከነዚህ ልዩነቶች የተነሳ ማንም ሊኮነንና ሊወገዝ አይገባም ፡፡ ይህ ከሆነ ግን የግጭትና ብጥብጥ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል ፡፡ ይልቁንም ልዩነቶቹ ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን የተናጥል ወይም የጋራ ጥቅም በእርጋታ መርምሮ ጥቅም ላይ እንዴት እንደሚውሉ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱ የስልጣኔ መገለጫ ነው ፡፡ ለዚህም ነው የሰለጠነው ዓለም ልዩነት ለዘላለም ይኑር የሚል መፈክር አንግቦ አብሮ እየኖረ ያለው ፡፡

        ልዩነቶች በየትኛውም የአኗኗር ደረጃ ላይ ያሉ የነበሩና የሚኖሩ ናቸው ፡፡ በጓደኛሞች ፣ በባለትዳሮች ፣ በቤተሰብ ፣ በማህበረሰብ ፣ በሀገርና በዓለማችን  ልዩነቶች እዚህም እዚያም አሉ ፡፡ እንደ ሀገራችን ያሉና የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ መኖሪያ በሆኑ ሀገራት ከሌላው በተለየ በርካታ ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ፡፡

       ለበርካታ ዓመታት ልዩነቶቻችንን ያየንበትና ያስተናገድንበት መንገድ የተሳሳተና ጽንፈኛ በመሆኑ ልዩነቶችን በኃይል ጨፍልቆ አንድ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ለኋላ ቀርነትና ለድህነት ዳርጎን ቆይቷል ፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ግን ልዩነት መብት እንጂ ሀጢያት ያለመሆኑን የሚያስተምር ፤ ይህንኑ መብት በህጋዊ መንገድ የሚያጎናጽፍ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ባለቤት በመሆናችንና ይህንኑ ህገ መንግሰት የሚጠብቅና የሚተገብር ፤ ልዩነቶችን ያለገደብ የሚያስተናግድ ህገ መንግስታዊ ሥርአት በመገንባታችን  ሁላችንም ተጠቃሚዎች የሆንበትን ዕድገት ልናስመዘግብ ችለናል ፡፡

        ለመሠረታዊ ችግራችን ፍቱን መፍትሄ ስላገኘን ከኋሊዮሽ ጉዞ ተላቀን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማምጣታችን ወደ ትራንስፎርሜሽንና ህዳሴ ዘመን ገብተናል ፡፡ ከነልዩነቶቻችን ህዳሴዋን በቅርብ እያማተረች መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምትተጋና የሁላችንም የጋራ መኖሪያ የሆነች ሀገር ባለቤቶች ሆነናነል ፡፡

       ስለዚህ ልዩነቶቻችንን በመከባበርና በመፈቃቀድ ስናስተናግዳቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንና የዕድገቶቻችን የኃይል ምንጭ እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ አይገባም!!!

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

ድሬዳዋ

13/05/2008ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here