የትኛውም መብት ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም

0
629

የሰው ልጆች መብቶች በመጀመሪያ ከህልውና ጋር በጥብቁ የሚቆራኙ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የሰው ልጆች በህይወት በመኖራቸው ምክኒያት የሚያስፈልጉ ሌሎችንም ጉዳዮችን ያጠቃልላሉ፡፡  በህገ-መንግስቱ ላይም ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ተብለው በግልጽ በየፈርጃቸው የተቀመጡ ስለሆነ ማንበቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ ሁለቱንም የመብት ዓይነቶች በወንጀል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ምንም ሳይጎድል እና ሳይሸራረፍ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ዜጎች ሁሉ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ያጎናጽፋቸዋል፡፡ ይህን ህገ-መንግስቱ ራሱ ሳያሻማ በግልጽ ስላስቀመጠው ለክርክር እና ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡

       ይሁን እንጂ ዜጎች በህገ-መንግስቱ የተጎናጸፏቸውን መብቶች ለመጠቀም  በተግባር ልምምድ ውስጥ ሲገቡ የሌላውን ዜጋ መብት መንካት ሲጀምሩ በህገ-መንግስቱ የተጎናጸፉት መብት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ በሌላ አባባል በህግ የተሰጣቸውን ሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብት በህግ ይነጠቃሉ ማለት ነው፡፡

       ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክኒያት ህግ-መንግስቱ በራሱ ለዜጎች መብቶችን ማጎናጸፍ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ዜጎች የህግ ከለላ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ስለሆነም የህግ-መንግስቱ ባህሪይ ስለሚያስገድድ ዜጎች በህገ-መንግስቱ የተጎናጸፉትን የትኛውም መብት ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መጠን እና መንገድ ብቻ  እንጂ ከዚያ ውጪ መጠቀም አይችሉም፡፡ ቢሞክሩም በህግ የሚጠየቁበት ሥርዓት በማንም ሊሻር አይችልም፡፡

       ስለ ዴሞክራሲ ምንነት እና ስለ መብቶቻችን አጠቃቀም የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዛችን አሊያም በቂ ዕውቀት ስለሌለን ከህግ ተጠያቂነት ልንድን አይችልም፡፡ የትኛውም ዜጋ መብቱን ያለአግባብ ተጠቅሞ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ሰብዓዊ መብቴ ነው ማለት አይችልም፡፡

       ምክኒያቱም ህግ በወንጀል የሚፈለገው ዜጋ ከላይ ከተጠቀሱት መብቶች የተወሰኑትን አሊያም ሁሉንም መብቶቹን ሊያጣ ስለሚችል ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉንም መብቶቻችንን በህጋዊ መንገድ ብቻ እንድንጠቀም በህገ-መንግስቱ እንገደደዳለን፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር የትኞቹም መብቶቻችን ከህግ በላይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       12/04/2011ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here