ለሠላም ስለሠላም የተከፈለውን ዋጋ ልናከብረው ይገባል

0
683

ለሁላችንም መተኪያ የሌላት እና የጋራ መኖሪያችን የሆነችውን ሀገር የመገንባቱ ኃላፊነት የሁላችንም ነው፡፡ ሀገርን የመገንባት አጀንዳዎቻችን ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ተጨማሪ ጊዜ ልናባክን አይገባም፡፡ ይህችን ሀገር ለመገንባት ትውልድ ሁሉ በየተራው ይሄ ነው ተብሎ እንዲህ በቀላሉ በአንደበት ሊገለጽ የማይቻል ትልቅ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ይህን ለሠላም ስለሠላም የተከፈለ ክቡር ዋጋ ማክብር እና ጠብቆ ማቆየት የአሁኑ ትውልድ የሞራል ግዴታ ነው፡፡

        ለሠላም መስፈን ዋጋ የከፈሉ አባቶቻችን ለራሳቸው ሠላም አጥተው እየተሠደዱ እና ጸረ ሠላም ኃይሎች ትግላቸውን እናዳያጨናግፉባቸው በብዙ ስጋት እየተንከራተቱ ከበረሀ በረሀ ከሀገረ ሀገር መከራ እየጠበሳቸው ለሚመጣው ትውልድ በማሰብ አልፈዋል፡፡ መጽናናታቸው እና ተስፋቸው  የሚመጣው ትውልድ ስለነበር ለከፈሉት ክቡር ዋጋ ለአፍታም አልተጸጸቱም፡፡

        ዛሬ ዛሬ ግን እየታየ ያለው ነገር ያለፈውን ትውልድ አደራ በክብር ተቀብሎ በማቆየት ለመጪው ትውልድ የማስተላለፉ ዋናው ቁም ነገር የተዘነጋ ይመስላል፡፡ የአባቶቻችን ከሀገር ሀገር መንከራተት፤ በረሀ ለበረሀ መንገላታት እና ሌላውም ህመማቸው የሚያመው ኑ በፍቅር እና በይቅርታ እንደመር ብሎ የሩቁንም የቅርቡንም በናፍቆት ይጣራል፡፡

        በሌላው ወገን ደግሞ አውቆም ሆነ ሳያውቀው ለፍቅር እና ለይቅርታ የተዘረጋን እጅ  በመንከስ መልካሙን ሥራ ለማጨናገፍ ይጥራል፡፡ ለመሆኑ ሀገርን አንዱ ሲገነባ ሌላው እያፈረሠ እስከመቼ መቀጠል ይቻላል፡፡ የአባቶቻችንን ድካም ገደል ጨምረን ከዚህ ተጋባራችን ሊጠቀም የሚችለውስ ማነው? እስቲ ቆም ብለን እናስብ፡፡

        አንዱ ትውልድ ከሌላው ትውልድ ጋር በራዕይ እና በጋራ ጥቅም መተሳሰሩ የስልጣኔ መገለጫ እንጂ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም፡፡ አዳዲስ ለውጦችን በፍጥነት የምናስተናግድበት ዘመን ላይ ብንገኝም ከአባቶቻችን ደግሞ የወረስናቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ በነጻነቷ ፣ በሉዓላዊነታ፣ እንዲሁም በአልበገርም ባይነቷ ታፍራ እና ተከብራ የኖረችን ሀገር አስረክበውናል፡፡ በአብሮነት እና በፍቅር ዘር፣ቀለም፣ሐይማኖት እና ሌሎችም ልዩነቶች ሳያግዷቸው ሰው በመሆናቸው ብቻ እንዴት መኖር እንደሚቻል አሳይተውናል፡፡

        ስለሆነም ለሠላም ስለሠላም የተከፈለውን ክቡር ዋጋ ጠብቀን፤ የራሳችንን አስተማማኝ የሠላም ሥራዎች በማከል  ለትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       19/04/2011ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here