የኋላችንን እየረሳን የፊታችንን ልንይዝ ይገባል

0
625

በህገ-መንግስቱ መግቢያ ላይ እንደ አንድ ሀገር ህዝብ ከዚህ ቀደም በመሀላችን የነበሩ የተሳሳቱ መስተጋብሮቻችንን በማረም እና በማስተካከል አንድ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መገንባት እንዳለብን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ሀሳብ ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው ያለፉ የተሳሳቱ ታሪኮቻችን እንዳይደገሙ ተምረን ነገን ለእኛም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ የተሻለ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባን የሚያሳስብ መልዕክት ነው ያለው፡፡

ከተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ በፊት  የመጣንብትን ተጨባጭ ሁኔታ ስናጠናው ግን የሚያሳየን እውነታ ህገ-መንግስቱ በሚያሳስበን ልክ አንድ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሄድንብት ርቀት ብዙም አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ አንድ የሚያደርጉን ሀገራዊ ጉዳዮች  ላይ ከማተኮር ይልቅ እነዴት መለያየት እንዳለብን የሚያጎሉ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተጠምደን ቆይተናል፡፡

ያለፉ አስቀያሚ ታሪኮቻችንን በማጉላት እና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የምንኮራበትን አርዓያ የአብሮነት ታሪካችንን በመዘንጋታችን  በመካከላችን ቂም፣ ጥላቻ እና ቂም በቀል ሊፈጠር ችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ እዚህም እዚያም በሚቀሰቀሱ ግጭቶች የሰው ህይወት እያለፈ ሌላ ጥላቻ እና ቂም እየተፈጠረ ነው፡፡ መልሰን የተሳሳቱ ታሪኮቻችንን እየደገምን የኋሊት መመለሱ ከዚህ ትውልድ ጀምሮ ሊያበቃ ይገባል፡፡

ለውጥ ያስፈለገን ፤ በፍቅር በይቅርታ እንደመር ብለን በጋራ ጉዞ የጀመርንበትም ዋናው ምክኒያት ለዚሁ ለተቀደሰ ዓላማ እና ግብ ሲባል ነው፡፡ ፍቅር በደልን አይቆጥርም ፡፡ ከልቡ ይቅርታ ያደረገ ደግሞ ወደ ነገው የበዳይ እና የተበዳይ ታሪክ አይመለስም፡፡ ይልቁንም በዳይ እና ተበዳይ አንተ ትብስ እኔ እብስ ተባብለው በዳይ ተበዳይን እንዴት እነደሚክስ፤ ተበዳይ ደግሞ እነዴት ፍቅራቸው ሊታደስ እንደሚችል ነው የሚያስቡት፡፡

ይህ ሲሆን ብቻ ነው ክፋት ሁሉ ጸጥ ብሎ ሠላም እና መረጋጋት የሚሰፍነው፡፡ አለበለዚያ ግን ውሀ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው እና ብሂሉ የተሳሳተን መጥፎ ታሪክ እየደጋገሙ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለው የኋሊት ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡

ስለዚህ አንደነታችንን፣ ዕድገታችንን እና ብልጽግናችንን የማይፈልጉ የጋራ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሚያራግቡትን ያን አስቀያሚ ታሪካችንን በመተው ነገን የተሻለ የሚያደርገውን ተስፋችንን እንያዝ፡፡

የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         24/03/2011ዓም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here