ለሠላማችን ሲባል ማድረግ ያለብንን ሁሉ ልናደርግ ይገባል

0
716

ሠላም ማለት ለእኛ ለኢዮጰያዊያን ካሳለፍነው እና አሁን ከምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እጅጉን አስፈላጊ እና የህልውናችን ጉዳይ ነው፡፡ የሠላም መረጋገጥ ከድህነት ለመውጣት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ ዋስትናችን ነው፡፡ በሀገራችን ታሪክ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለን ተስፋ የጣልንበት የለውጥ ጉዞ ከዳር የሚደርሰው ሠላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡

 ዴሞክራሲው ጎልብቶ እና መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ዜጎች በዚህች ሀገር የተሸለ ኑሮ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉት አስተማማኝ ሠላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ባጠቃላይ ሠላም ከሌለ ምንም መልካም የሚባል ነገር ሁሉ አይኖርም፡፡ ከዚያ ይልቅ በተቃራኒው ለቅሶ፣ ሀዘን፣ ዋይታ እና እንጉርጉሮ ወ.ዘ.ተ ተንሰራፍቶ የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱን ከድህንት እና ኋላቀርነት ጋር ይቀጥላል፡፡

ሠላም ካለ ሁላችንም አሸናፊዎች እንሆናለን፡፡ ሠላም በሌለበት ግን ማንም ሳያሸንፍ  አሸናፊ በሌለበት ብጥብጡ  ይቀጥላል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለሠላም አስፈላጊነት ከሚነገረን በላይ በተግባር የምናውቀው ይበልጣል፡፡ ምክኒያቱም ሠላም ባጣንባቸው ወቅቶች ሁሉ ሀዘን እቤቱ ያልገባ የለም፡፡ ስለሆነም ስለሠላማችን ሲባል ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ እና መክፍል ያለብንን ሁሉ መስዋዕትነት ልንከፍል ይገባል፡፡

በህገ-መንግስቱ የተጎናጸፍናቸው መብቶቻችን ለሌላውም ዜጋ በእኩልነት የተሠሰጡ ስለሆነ መብቶቻችንን ስንጠቀም ለሌላውም ዜጋ በማሰብ በህጋዊ መንገድ ብቻ ልንጠቀም ይገባል፡፡ ይህች መተኪያ የሌላት የጋራ መኖሪያችን ተሳስበን እና ተከባብረን የምንኖርባት እንጂ በመናናቅ እና በማንአለብኝነት የምናፈርሳት ልትሆን አይገባም፡፡

ሁሉም በየእምነቱ፣ በየባህሉ እና ወጉ ሌባን፣ ዘራፊን፣ አጥፊን እና ሠላምን የሚያደፈርሰውን የሚቀጣበት ሥርዓት አለው፡፡ ይህን የቆየ መልካም እሴታችን ስለሆነ አጠናክረን በማስቀጠል የህግ የበላይንት እንዲሰፍን የበኩላችንን አስትዋጽኦ ልናበረክት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል በማስረጃ ወንጀለኝነቱ የተረጋገጠበት ወንጀለኛን የሚያስተምር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚቀጣ ሁላችን ካጸደቅነው ህግ-መንግስት የተቀዳ ህግ አለ፡፡ በዚህ ህግ ፊት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል መሆኑ በህገ-መንግስቱ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ወንጀለኛ ወንጀለኝነቱ ሲረጋገጥ ብሄሩ፣ ሀይማኖቱ እና ከየትኛው ወገን እንደሆነ ማንም ሊጠይቅ አይገባም፡፡ ወንጀለኛ ወንጀለኛ ነው፡፡

የትኛውም ብሄር፣ ሐይማኖት እና ወገን የወንጀለኛ መደበቂያ ሊሆን አይፈልግም፡፡ ስለዚህ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ተባባሪ እንጂ ወንጀለኝነቱን ትተን ማንነቱን ብቻ በማየት ስናውቀውም ሳናውቀውም አደናቃፊ ላለመሆን ቁርጠኛ አቋም ልንይዝ ይገባል፡፡ ለሠላም ሲባል፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       14/03/2011ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here