ሴቶች የማህበረሰብ ድርሻቸውን በሚገባ ሊወጡ ይገባል

0
659

ሴቶች በማህበረሰቡ መሀል ያላቸው የመምራት ኃላፊነት ድርሻ ድርብ እና ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት የሚጀምረው የሀገር እና የህዝብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰብን መምራት ምን ያህል አንደሚከብድ የሚታወቀው በሆነ አጋጣሚ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት ሴቶች ከቤተሰብ ተለይተው ሲቆዩ ነው፡፡ ለዚህ ዋና እማኝ የሚሆኑት ሁኔታው ያጋጠማቸው አባወራዎች ናቸው፡፡

የሴቶች የመምራትና የኃላፊነት ድርሻ በቤተሰብ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የቤተሰቡንም የወጪ ክፍተት ለመሸፈን በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ በሚያደርጉት ጥረትና የቤተሰቡን ወጪ በማብቃቃት እና በታማኝነት መምራት ላይም በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህ ሴቶች የአንድ ቤተሰብ የጀርባ አጥንት ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በዚህ ሳይበቃ ሴቶች በእድር በማህበሩ የሚጫወቱት ሚና በማንም ሊተካ አይችልም፡፡ ዕድርን እና ማህበርን ከመምራት ጀምሮ በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ሰዎችን ለጋራ ተጠቃሚነት እስከ ማሰባሰብ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ናቸው፡፡ በሁሉም ሁኔታና አካባቢ የሴቶች ታማኝነትና ሥራን በኃላፊነት ስሜት የመሥራት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡

አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሴቶች ሀገር ከመምራት አንጻር በከፍተኛ አመራርነት ያላቸው ተሳትፎ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሃምሳ በመቶ ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊት በሴቶች ይደፈራሉ ተብሎ በማይገመቱ የአመራርነት ቦታዎች ሳይቀር በኃላፊነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የህ የሆነው በድንገት ሳይሆን ከላይ ለመዘርዘር እንደተሞከረው ሴቶች የድርብ ኃላፊነትና ልምድ ባለቤቶች በመሆናቸው ነው፡፡

ይህን ትልቅ ሀቅ ማህበረሰቡም ሆነ ሴቶች እራሳቸው በሚገባ ሊገነዘቡት እና በተረዱት ልክ ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ ለሠላሙ ለልማቱ እና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሴቶች ይህን በብዙ ድርብ ኃላፊነት የዳበረ ልምዳቸውን ከቤተሰብ ጀምረው እስከ ማህበረሰብ የበኩላቸውን የማይተካ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡

በተለይ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ የሆነውን ሠላም ከማረጋገጥ አንጻር የቤተሰብ ወጣቶችን ከዚያም የአካባቢ ወጣቶችን ከማስተማር እና በኃላፊነት ስሜት እንዲቀሳቀሱ የማድረግ  ኃላፊነትን ሴቶች በተደራጀ መልኩ እና በተናጥል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         10/03/2011ዓም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here