ነገን የተሻለ ለማድረግ ወጣቱ ግንባር ቀደም ሚናውን ሊጫወት ይገባል

0
806

የወጣትነት ዕድሜ ችኩልነት፣ ለአዳዲስ ነገሮች መጓጓት እና ሁሉን ነገር ደፍሮ በተግባር ለማየት የሚፈለግብት ዕድሜ ነው፡፡ እነዚህ የወጣትንት ዕድሜ መገለጫ ባህሪያት በአግባቡ ተገርተው ጥቅም ላይ ካልዋሉ የራሳቸው ጎጂ ጎን አላቸው፡፡ በዚህ ዕድሜ በችኮላ የሚወሰኑና የሚደረጉ ተግባራት ሁሉ ፍጻሜያቸው የዕድሜ ልክ ጸጸት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከዛሬ አልፎ ነገን አሻግሮ በማየት ሰከን ብሎ መወሰን እና ውሳኔን ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ የወጣትነት ዕድሜ ትልቅ ታሪክ የሚሠራበት ዕድል ነው፡፡ ምክኒያቱም ዛሬ በማስተዋል የተዘራ ዘር ነው ነገ በኩራት የሚታጨደው፡፡ ይህ ዕድሜ ታሪክ ከማውራት ይልቅ ታሪክ የሚሠራበት በመሆኑ ወጣቶች ይህን ትልቅ ዕድል እና አጋጣሚ እንዲባክን መዘናጋት የለባቸውም፡፡ ነገ በኩራት ለመጪው ትውልድ የሚናገሩት እና የሚያወርሱት የራሳቸው በጎ ታሪክ እንዲኖራቸው ዛሬ በእርጋታ ሊያስቡ ይገባል፡፡

ስለሆነም አፍላ ጉልበታቸውን እንደ ነቀዝ ከሚበላ አልባሌ ቦታ እና ልምምድ ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ትኩስ እና ፈጣን አዕምሯቸውን ከሚያላሽቅ ተስፋ አስቆራጭ አስተሳሰብ ብሎም ድርጊት ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው፡፡ ጠባብንት፣ ትምክህኝንት፣ ግለኝንት፣ አክራሪነት እና ወ.ዘ.ተ ለሀገርም ለወገንም የማይጠቅሙ አመለካከቶች ከተጠናወቷቸው የታሪክ ተወቃሾች ራሳቸውን ሊያርቁ ይገባል፡፡

ከዚያ ይልቅ ምክኒያታዊ በሆነ በሳል አስተሳሰብ ሀሳቦችን እና ተግባሮችን በምክኒያት የመደገፍ፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ በምክኒት  የመቃወም እና የመኮነን ልምድን ማዳበር ይገባቸዋል፡፡ ከአባቶች የተረከቧቸውን አኩሪ ገድሎች በመጠበቅ እነሱ ደፋ ቀና ብለው አዚህ ያደረሷትን ሀገር በመረከብ ነገን የተሻለ ለማድረግ የወጣትነታቸውን ዕድሜ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ ስለሆነ አሁን ባለተራ የሆነው ወጣት ባለማወቅ እና በችኩልነት ከላይ ለመጥቀስ በተሞከሩት አፍራሽ አመለካከቶች በመሰለብ  ሀገር እንዳያፈርስ ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡ ነገን የተሻለ የማድረግ እና  ያለማድረግ ኃላፊነቱ የወደቀው በወጣቱ እጅ ነው፡፡

አባቶች  በተፈጥሮ  ሂደት አቅማቸው እየደከመ ማንም የማይቀርበት ሞት ከመምጣቱ በፊት የደከሙበትን የሀገር ጉዳይ የሚረከባቸው ወጣቱ ስለሆነ ተስፋቸውን የሚጥሉት በወጣቱ ላይ ነው፡፡ ይህን ምን ጊዜም የማይሻር ሀቅ ወጣቱ በውል ሊገነዘብ እና ባለበት ከባድ ኃላፊነት ልክ ነገን የተሻለ ለማድረግ ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡

የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         21/03/2011ዓም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here