ለዘመናት ዋጋ ከፍለን የደከምንበትን የሀገር ጉዳይ ማን ይረከብ ?

0
657

ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ እንጂ በአንድ ትውልድ ብቻ ተገንብቶ ያለቀለት ሀገር በዚህ ምድር ላይ የትም አይገኝም፡፡ ስለሆነም ካለፈው ትውልድ ያለው ትውልድ ያላለቀ የሀገር ሥራን እየተረከበና ከውድቀታቸውና ከስኬታቸው እየተማረ ሁሉም በተራው አደራውን ሲወጣ ነው ሀገር እዚህ የደረሰችው፡፡

ልብ ልንለው የሚገባው ሁሉም በየተራው የደከመው ግን አንዲት መተኪያ የሌላትን ሀገር ለመገንባት ነው፡፡ ባለአደራው ትውልድ መክፍል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ የተፈጥሮ ህግ ነውና ዕድሜ ሲጫጫን፤ ጀምበር ስታዘቀዝቅ፤ የሚያሳስበው ጉዳይ የሀገር ጉዳ እንጂ ሌላም አይደለም፡፡ አዎ ትውልድ በየተራው ትልቅ ዋጋ የከፈለበትን የሀገር ጉዳይ ማን ይረከብ ?ይህ የአደራ ቅብብሎሽ ትላንትናም ነበር ዛሬም አለ ነገም ይቀጥላል፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ሊወቀስም ሊመሰገንም የሚችል ትውልድ ይኖራል፡፡ አንዳንድ ትውልድ የራሱን አደራ ተወጥቶ ለመጪው ትውልድ የቤት ሥራ ያመቻቻል፡፡ በዚህም ተተኪው ትውልድ እያመሰገነው ቢሞትም ከመቃብር በላይ ይኖራል፡፡ አንዳንድ ትውልድ ደግሞ ባገኘው ዕድልና ዕድሜ የራሱን ጥቅም ብቻ ሲያሳድድ ለቀጣዩ ትውልድ ተጨማሪ የቤት ሥራ ትቶ ጊዜና ሀብት አባክኖ ያልፋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የታሪክ እና የትውልድ ተወቃሽ በመሆን ሁለተኛውን ሞት ይሞታል፡፡

አሁን ያለው ተውልድ ቆም ብሎ ለመጪው ትውልድ ስለሚያወርሰው ነገር ደጋግሞ ማሰብ አለበት፡፡ ድህንት፣ ኋላቀርነት፣ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህት፣ ጥበት፣ዘረኝነት የሀይማኖት አክራሪነት በጭራሽ ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዳይሻገሩ አቅምን አሟጦ ሊሠራ ይገባል፡፡ በጥላቻ እና በቂም በቀል ላይ ከከፈትነው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ባልተናነሰ ደረጃ በእንዚህ ላይም የተጠናከረና ቀጣይነት ያለው ዘመቻ መክፈትና መረባረብ የምን ጊዜም ትኩረታችን ሊሆን ይገባል፡፡

በአመለካከትና በተግባር እዚህም እዚያም ብቅ እያሉ የጠፉ እየመሰሉ ተመልሰው   እንደገና የሚያገረሹትን እነዚህን ሀገርንና ህዝብን የሚያጠፉ አመለካከትና ተግባራት  መዋቅሮችን የመበጣጠስ ሥራ ቀጣይነቱ ትኩረት ሊሠጠው ይገባል፡፡ የፍቅር፣የይቅርታና የመደመር የለውጥ ጉዟችንን በማጠናከር ለመጪው ትውልድ በጎ በጎውን እንጂ መጥፎ መጥፎውን ወደሚቀጥለው ትውልድ እንዳይሸጋገሩ ዙሪያ መለስ ርብርብ ልናደርግ ይገባል፡፡

    እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ተግባራትና አመለካከቶች በተያያዝነው የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ  ግስጋሴ ፊት የተደቀኑ ፈተናዎች መሆናቸውን በተደጋጋሚ ካሳለፍናቸው ተሞክሮዎች በተግባር ለመመልከት ችለናል፡፡ እነዚህን ፈተናዎች በብቃት ለመወጣት አምርሮ የህግ የበላይነትን ማስከበሩ እንዳለ ሆኖ ትውልድን ማንቃትና ማስተማር ይገባል፡፡

        ምክኒያቱም ያለማናትን፣ ሠላሟ እንዲረጋገጥ ብዙ ዋጋ የተከፈለላትንና ህዳሴዋን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና የምንልላትን መተኪያ የሌላትን ሀገር የምናስረክበው ለሀገሩም ለወገኑም ታማኝ ለሆነ ትውልድ ሊሆን ይገባል፡፡

 የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         26/02/2011ዓም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here